የህዝብ ጥያቄዎችን ለመመለስ የተጀመሩ ህዝባዊ ውይይቶች ቀጣይነት ሊኖራቸው ይገባል...የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች

57
ሚዛን ነሀሴ 2/2010 የህዝብ ጥያቄዎችን አድምጦ ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዲቻል መንግስት የጀመራቸው ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ቀጣይነት ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ። ነዋሪዎቹ ከደኢህዴን ሊቀመንበር ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል ጋር በወቅታዊና በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል። ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ወጣት ሰኢድ ኢብራሂም እንዳለው መድረኩ ሀሳባቸውን በነጻነት ከማቅረብ ባለፈ የተሻለ መግባባት የታየበት እንደነበረ ገልጸዋል። "ሀሳባችንን በነጻነት የምንገልጽበት መድረክ ስንፈልግ ቆይተናል፤ መንግስት በአዲስ አካሄድ ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት መወሰኑ የሚበረታታ  ነው"  ብሏል፡፡ መሰል የውይይት መድረኮች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የተናገረው ወጣቱ ይህም የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ ተረድቶ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግሯል፡፡ " የዜጎችን ሀሳብ በነጻነት የመግለጽ ዕድል መበረታታት አለበት " ያሉት ሌላው የውይይቱ አስተባባሪና ተሳታፊ አቶ አለማየሁ ካፒቶ ናቸው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበሩ የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንግስትና ተገልጋዩ ህዝብ ተቀራርበው ባለመስራታቸው የተፈጠሩ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት ዜጎች በነጻነት ሀሳብ የሚሰጡበት መድረክ መዘጋጀቱ ይህንን ችግር እንደሚያቃልለው ተናግረዋል፡፡ የውይይት መድረኩ ነጻና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር የገለጹት አቶ አለማየሁ በመድረኩ መንግስት ያሉበትን የአሰራር ውስንነቶች በአግባቡ እንዲያውቅ መደረጉንና ይህም ፈጥኖ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችለው መሆኑን ተናግሯል፡፡ በአካባቢያቸው ዘርፈ ብዙ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች መኖራቸውንና ምላሽ ሳያገኙ መቆየታቸው በመድረኩ አንስተው ውይይት መደረጉን የገለጹት ደግሞ አቶ ታጠቅ ታጋይ ናቸው፡፡ መንግስት እንደጉዳዮቹ ክብደትና ደረጃ አይቶ ተገቢ ምላሽ መስጠት እንዳለበት የገለጹት አቶ ታጠቅ፣ የህዝብን ጥያቄ ለይቶ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት መንግስት የጀመራቸውን ህዝብ የማወያየት ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ አመልክተዋል። አቶ ታጠቅ እንዳሉት ሰሞኑን እየተካሄደ ያለው ሕዝባዊ የምክክርና የውይይት መድረክ በህዝብ ችግሮች ላይ በጋራ ከመምከር ባለፈ ተጠያቂነትን ለማስፈን ያስችላል፡፡ በሁሉም አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ተረድቶ ህዝብን በአግባቡ የሚመራ ብቁ አመራር ማስቀመጥ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የደኢህዴን ሊቀመንበር ክብርት ወይዘሮ ሙፈርያት ካሚል በቅርቡ በደቡብ ምዕራብ ዞኖች ከካፋ፣ ሸካና ቤንች ማጂ ዞን ነዋሪዎች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸው ይታወሳል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም