በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን በማስመለስ ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉደተኞች ሊሰጡ ይገባል - የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዎች

62
ደብረብርሃን ነሀሴ 2/2010 በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን በማስመለስ ለአቅመ ደካሞችና አካል ጉደተኞች ሊሰጡ እንደሚገባ የደብረብርሃን ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ። የከተማው አስተዳደር በበኩሉ በጉልበትና በህገ-ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን ለይቶ ለሚገባው ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጿል፡፡ በደብረብርሃን ከተማ የ04 ቀበሌ ነዋሪ አቶ ሀይለስላሴ ጌታነህ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት በየቀበሌው የግለሰብ ቤት ተከራይተው ለመኖር የማይችሉ አቅመ ደካሞች፣ አረጋዊያን፣ ሴቶችና ሌሎች ግለሰቦች እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ በከተማው የሚገኙ የቀበሌ ቤቶች ደግሞ በህገወጥ መንገድ ተይዘው እንደሚገኙ ገልፀዋል። በመሆኑም በከተማው በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን በማስመለስ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች የቤት ባለቤት ማድረግ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡ የ09 ቀበሌ ነዋሪ መቶ አለቃ ከፈለኝ ወልደፃዲቂ እንደገለጹት የቀበሌ ቤቶቹ በአመራሮችና የግል ቤታቸውን አከራይተው በሚጠቀሙ ግለሰቦች ተይዘዋል። በከተማዋ በርካታ ሰው የዕለት ጉርሱን ሳይሞላ ጾሙን እያደረና በቤት ኪራይ እየተሰቃየ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ቤታቸውን አከራይተው በቀበሌ ቤት የሚኖሩትንና በቂ ገቢ ያላቸውን መንግስት ለይቶ ቤቱን በማስመለስ ለሚገባቸው ሰዎች እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡ በህገ ወጥ መንገድ  ቤት የያዙትን በማጋለጥ በኩል የሚጠበቅባቸውን ድርሻ እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡ የደብረብርሃን ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አክሊሉ ጌታቸው በበኩላቸው በከተማው በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ በርካታ የቀበሌ ቤቶች መኖራቸውን አምነዋል፡፡ ችግሩን መስተዳድሩ መፍታት ባለመቻሉ አንዱና ዋናው የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ሆኖ መቆየቱንም ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ለችግሩ እልባት ለመስጠት በቀበሌ ቤቶችና አያያዛቸው ላይ የማጣራት ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ እስካሁን በተሰራው ስራ በማይገባውና በህገወጥ መንገድ የተያዙ 89 የቀበሌ ቤቶች መለየታቸውን ጠቁመው በቀጣይ የማጣራት ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡም በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶችን በማጋለጥና ከመንግስት ጎን በመቆም መብቱን ለማስጠበቅ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡ በከተማው ከ2 ሺህ በላይ የቀበሌ ቤቶች መኖራቸውን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም