የከተማ ነዋሪዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ ህዝባዊ ወገንተኝነት ተላብሶ ሊሰራ ይገባል - አቶ ጃንጥራር አባይ

125
በህርዳር ነሃሴ 2/2010 የከተማ ነዋሪዎችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አመራሩ ህዝባዊ ወገንተኝነት ተላብሶ ሊሰራ እንደሚገባ የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ። በከተማ ልማት ቤቶችና ኮንስትራክሽን አመራሮችና ባለሙያዎች የተሳተፉበትና በከተሞች እድገትና በህዝብ ተጠቃሚነት ላይ ያተኮረ የ15 ቀናት ስልጠና በባህርዳር ከተማ ተጀምሯል። በስልጠናው መክፈቻ ላይ ሚኒስትሩ አቶ ጃንጥራር አባይ እንደገለጹት ኪራይ ሰብሳቢነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መጓደል በአገሪቱ በሚገኙ ከተሞች የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው ። በአማራ ክልል በሚገኙ ከተሞችም ከመሬት፣ ከግብር፣ ከመልካም አስተዳደር እጦት፣ አገልግሎት አሰጣጥና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ችግር እንደሚነሳ ተናግረዋል። በመሆኑም የአመራሩንና የፈጻሚውን እውቀትና ክህሎት በማጎልበት ህዝባዊ ወገንተኝነት ተላብሶ እንዲሰራ ማድረግ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል። አሁን በተጀመረውና ለቀጣይ 15 ቀናት በሚቆየው የዘርፉ አመራሮችና ባለሙዎች ስልጠናም ሳይንሳዊና ዘመናዊ እውቀትን በመጨበጥ ሰልጣኞች ለቀጣይ ስራ እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስበዋል። የአማራ ክልል ከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ፈንታ ደጀን በበኩላቸው ''በከተሞች የሚስተዋለው የስራ አጥነት፣ ድህነትና የመልካም አስተዳደር ችግር አመራሩ በህዝባዊነት ስሜት ሊሰራ ባለመቻሉ የተከሰተ ነው'' ብለዋል። የስልጠናው ዓላማም በክህሎት የዳበረና ተነሳሽነት ያለው አመራር ለመፍጠር እንደሆነ ጠቁመዋል። ዘሬ በተጀመረው ስልጠና ላይ በአማራ ክልል ከሚገኙ 42 የከተማ አስተዳደሮችና 233 ማዘጋጃ ቤቶች የተውጣጡ ከ600 በላይ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም