የደቡብ ሱዳን መንግስትና ተቃዋሚ ኃይሎች የፈረሙትን የሰላም ስምምነት በታማኝነት እንዲተገብሩ የአፍሪካ ህብረት አሳሰበ

54
አዲስ አበባ ነሃሴ 2/2010 የደቡብ ሱዳን መንግስትና ተቃዋሚ ኃይሎች ሰሞኑን የፈረሙትን የሰላም ስምምነት በታማኝነትና በቁርጠኝነት እንዲተገብሩ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋቂ ማሀማት አሳሰቡ። የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ማያርዲትና የተቃዋሚ ቡድኑ መሪ ዶክተር ሪክ መቻር ሐምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም በሱዳን ካርቱ የአስተዳደርና ስልጣን ክፍፍል ጉዳዮች ላይ ስምምነት መፈረማቸው የሚታወስ ነው። የደቡብ ሱዳን ፖለቲካ ተቀናቃኝ ወገኖች የደረሱት ስምምነት የአገሪቱን ግጭት በመግታት በህዝቡ ላይ እያስከተለ ያለውን መከራ ለማስቆም የሚያስችል ትልቅ እርምጃ መሆኑን የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ገልፀዋል። ተቀናቃኞቹ ለአገራቸው በመቆርቆር መንፈስ መስራት እና የገቡትን ቃል ኪዳን በማክበር ስምምነቱን በታማኝነትና በቁርጠኝነት መተግበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። የደቡብ ሱዳን ህዝብ በግጭቱ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ እንደተሰቃየ ያመለከቱት ሊቀመንበሩ ለዘላቂ ሰላምና ደህንነት በህዝቡ ዘንድ ያለውን ፍላጎት ማሳካት ለሌላ ጊዜ የሚተላለፍ ጉዳይ እንዳልሆነ ገልጸዋል። የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽርና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) አባል አገሮች መሪዎች በደቡብ ሱዳን ሰላም፣ ደህንነትና እርቅ እንደሚመጣ ላከናወኑት ተግባር አድናቆታቸውን ገልፀዋል። የኢጋድ አባል አገሮች የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖችን  እንዲያደራድሩ የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽርን መወከሉ ግጭቱ ቆሞ የሰላም ስምምነቱ እንዲተገበር ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ እንደሆነ ሙሳ ፋቂ ተናግረዋል። በኢጋድ አማካኝነት በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት የአፍሪካ ህብረት በተለያየ መንገድ እያገዘ መሆኑንም ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል። ይኸው ድጋፍ የሚቀጥል መሆኑንም ጠቅሰዋል። የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ቡድኖች በዋና ዋና የአስተዳደርና ስልጣን ክፍፍል ጉዳዮች ላይ በካርቱም የደረሱበትን ስምምነት አድንቋል። ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ተቀናቃኞቹ እንዲተገብሩ፤ በአገሪቱ አጠቃላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ በቁርጠኝነተ እንዲሰሩም ምክር ቤቱ አሳስቧል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም