ኩዌት ለኢትዮጵያ የምታደርገውን ድጋፍ ትቀጥላለች - የአገሪቱ አምባሳደር

91
አዲስ አበባ ነሃሴ 2/2010 የኢትዮጵያ መንግስት የአገሪቱን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያደርገውን ጥረት ኩዌት እንደምትደገፍ በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ረሺድ አል ሃጂሪ ተናገሩ። የሥራ ጊዜያቸውን ያጠናቀቁት አምባሳደር ረሺድ አል ሃጂሪ ይህንን የገለፁት ዛሬ የስንብት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ካቀረቡ በኋላ በሰጡት መግለጫ ነው። አምባሳደሩ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ኩዌት የሚቻላትን ድጋፍ ታደርጋለች። አገራቸውን ወክለው በኢትዮጵያ ባሳለፉት የሥራ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት የሚያስፈልገውን ድጋፍ እና ትብብር እንዳደረገላቸውም አምባሳደሩ አመልክተዋል። በኢትዮጵያ የሚካሄዱ የልማት እንቅስቃሴዎችንም የኩዌት መንግስት የሚደግፍ መሆኑን ተሰናባቹ አምባሳደር ጨምረው ገልፀዋል። በፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የኮሙኒኬሽንና ፕሮቶኮል ዳይሬክተር አቶ አሸብር ጌትነት ኢትዮጵያ ከኩዌት ጋር ያላት ወዳጅነት በአረብ አገራት ያላትን አጋርነት ዋነኛ ማሳያ ተደርጎ እንደሚወሰድ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ልማት ደጋፊ ከሆኑት አገራት መካከል ኩዌት ተጠቃሽ ናት ያሉት አቶ አሸብር፤ የኩዌት ፈንድ በቦሌ ዓለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማስፋፊያ ፕሮጀክት እያከናወነ ያለውን ድጋፍ ለአብነት አንስተዋል። ኢትዮጵያና ኩዌት የቆየ የንግድ ትስስር ያላቸው አገራት ሲሆኑ፤ ኢትዮጵያ በዋናነት የቅባት እህሎችና ስጋ ለኩዌት ታቀርባለች። በአንጻሩ ኢትዮጵያ ነዳጅና የህክምና መገልገያዎችን ከኩዌት እንደምታስገባ ከንግድ ሚንስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም