ይበልጥ ተደማጭነት ያላት ኢትዮጵያን ለመገንባት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸው የጎላ ነው — ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም

1000

ደብረ ማርቆስ/ እንጅባራ፤ ሐምሌ 17/2013 (ኢዜአ) ”የበለጸገች እና አለማቀፋዊ ደረጃ ይበልጥ ተደማጭነት ያላት ኢትዮጵያን እውን ለማድርግ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸው የጎላ ነው” ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደማሪያም ገለጹ።

ደብረ ማርቆስና እንጅባራ ዩኒቨርሲቲዎች ዛሬ ተማሪዎቻቸውን አስመርቀዋል።

በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ምረቃ ስነ-ስርዓት የተገኙት ፕሮፌሰር ሂሩት እንዳሉት፤ ዩኒቨርስቲዎች የሚያፈሯቸው ምሩቃን ሀገሪቱ የያዘችው የልማት እቅድ እውን እንዲሆን ሙያቸውን ተጠቅመው ሳይሰለቹ መስራት ይጠበቅባቸዋል።

የዩኒቨርሲቲዎች የትምህርትን ተደራሽነት ከማረጋገጥ በተጨማሪ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የታገዘ የፈጠራ ስራዎችን የሚያሳድግ ትውልድ ማፍራት ላይ ማተኮር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በአለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ተደማጭነት ያላት ኢትዮጵያን እውን ለማድርግ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ፕሮፌሰሯ ገልጸዋል።


”የተማረ ማለት ለሀገሩ የሚያስብ እና ለነገሮች ፈጥኖ መልስ ሊሰጥ የሚችል ማለት በመሆኑ እናተም በዚህ ልክ የተማራችሁትን ተግባር ላይ ማዋል ይጠበቅባችኋል” ሲሉም አሳስበዋል።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ታፈረ መላኩ በበኩላቸው፤ ዛሬ በመደበኛና መደበኛ ባልሆነ የትምህርት ፕሮግራም የሰለጠኑ 3 ሺህ 712 ተማሪዎች በመጀመሪያና ሁለተኛ ዲግሪ ማስመረቃቸውን አስታውቀዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርትን ሽፋን ተደራሽነት እምርታዊ ለውጥ እያስመዘገበች ነው ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲም በየጊዜው የሚቀበላቸውን ተማሪዎች በእውቀት፣ ክህሎት እና አመለካከት ብቁ እና ተወዳደሪ እንዲሆኑ ሰላማዊ እና ምቹ የማማር ማስተማር ሂደቶችን እየተገበረ  እንደሚገኝ ተናግረዋል።

”ተመራቂዎች በምትኖሩበትና በምትሰሰማሩበት የስራ መስክ ሁሉ ሰብዓዊነትን የህይወታችሁ መርህ በማድርግ ሀገራችን ከገባችበት ውስብስብ ችግር እንድትላቀቅ የራሳችሁን ገንቢ ሚና መጫወት ይገባችኋል” ብለዋል።

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ባለፉት አመታት ከ41 ሺህ በላይ ተማሪዎችን አስተምሮ ማስመረቁም ተመልክቷል።

በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ስነ ስርዓት የተገኙት የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዲላሞ ኦቶሬ፤ኢትዮጵያ አሁን ላይ የሥራ ገበያ በሚፈልገው መጠን ብቃትና ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል አቅርቦት በተፈለገው ደረጃ ያለመሆን ክፍተት እንዳለ ተናግረዋል።

በየዓመቱ በአማካይ ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎች ከመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ቢመረቁም አብዛኞቹ የመንግስት ሥራ ይጠብቃሉ ብለዋል።

ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ያገኙት ዕውቀትና ክህሎት በሥራ ገበያ ላይ በመተግባር ህዝባቸውንና ሃገራቸውን መጥቀም እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ከ100 ሚሊዮን የሚበልጥ ህዝብ ባለባት ሀገር የትምህርት ጥራትና ተገቢነትን ማስጠበቅ ለመንግስት ወሳኝ የፖሊሲ አጀንዳ ሊሆን እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲዎች የፖሊሲ አቅጣጫ የሚያሳኩ፣ ዕውቀትን መሠረት ያደረጉ የትምህርት ፕሮግራሞችን መክፈት እንዳለባቸው አመልክተው፤ ተመራቂዎችንም ከዘመን ጋር የሚሄድ አስተሳሰብ በማዳበር አዳዲስ ፈጠራዎች ላይ እንዲሳተፉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

እንጅባራ ዩኒቨርሲቲ  አዲስ ቢሆንም ከተልዕኮ አንፃር አግባብነትና ፍትሃዊነት ያለውን ትምህርት ለመስጠት በትኩረት እየሰራን ነው ያሉት ደግሞ የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጋርዳቸው ወርቁ ናቸው።

በ2010 ዓ.ም በ1ሺህ 500 ተማሪዎች በመቀበም ማስተማር  የጀመረው ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ በመደበኛ፣ በተከታታይና በክረምት ፕሮግራሞች ከ14 ሺህ በላይ ተማሪዎች እንዳሉት አመልክተዋል።

እንደ ዶክተር ጋርዳቸው  ገለፃ፤ በዩኒቨርሲቲው ምሁራን እየተሰሩ ካሉት 102 የምርምር ሥራዎች ውስጥ 56ቱን ያጠናቀቀ ሲሆን 46ቱ ደግሞ ሂደት ላይ ናቸው።

ዩኒቨርስቲው በተለያዩ የትምህርት ፕሮግራሞች በመጀመሪያ ዲግሪ ለሁለተኛ ጊዜ ያሰለጠናቸው 1ሺህ 74 ተማሪዎችን ዛሬ አስመርቋል።