ወያኔ ያወጀብንን ጦርነት ለመቀልበስ የክልሉ ነዋሪ ህዝብ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ይጠበቅበታል--- ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ

88

ሰመራ፤ ሐምሌ 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) ሁሉም የክልሉ ነዋሪ ህዝብ አሸባሪው ወያኔ ያወጀብንን ጦርነት ለመቀልበስ አካባቢውን በንቃት ከመጠበቅ ጀምሮ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ይጠበቅበታል ሲሉ የአፋር ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባ ገለጹ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ዛሬ ከሰመራ፣ ሎግያና ዱብቲ ከተማ ወጣቶች ጋር ተወያይተዋል።


ርዕሰ መስተዳድሩ  በውይይቱ ማጠቃለያ  ላይ እንደተናገሩት፤ የወያኔ ጁንታ ሀገሪቱን  እኛ ካልገዛን እናፈርሳታለን በሚል እብሪት ተወጥሮ  የአፋር ክልልን ጨምሮ በተለያዩ ግንባር የጥፋት ድርጊት እየፈጸመ ይገኛል።


የአፋር ክልላዊ መንግስትና ህዝብ በመከላከያ ሠራዊትና በሀገር ላይ የተቃጣ የእብሪት ጥቃት በራሱ ላይ የተፈጸመ መሆኑን በመገንዘብ በተጀመረው የህግ ማሰከበር እርምጃ ተገቢውን ንቁ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።


በዚህም እርምጃ የተደናገጠውና ተስፋ የቆረጠው የህወሃት ጁንታ በቅርቡ አፋር አርብቶ አደሮች ላይ በከፈተው ጦርነት በንጹሃን ህጻናት፣ ሴቶችና አረጋውያን እንዲሁም ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ጠቅሰዋል። 


ይህም ለአፋር ህዝብ ያለውን ንቀት በግልጽ የሚያሳይ ክብረ- ነክ ተግባር በመሆኑ የክልሉ ህዝብና መንግስት ከሀገር መከላከያ ሠራዊታችንና ሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በጥምረት የጁንታውን ግብአተ-መሬት ያፋጥነዋል ብለዋል።

ለዚህ የህልውና ዘመቻ ስኬታማነት ህዝብ አካባቢውን ከመጠበቅና  ስንቅ አቅርቦትን ጨምሮ ለጸጥታ ሃይሉ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።


በተለይም ወጣቶች ነጻነት በነጻ የማይገኝ  መሆኑን አውቀው በተጀመረው ሀገር የማዳን ዘመቻ የአካባቢያቸውን፣ ክልላቸው ብሎም ሀገራቸውን ሉአላዊነት የማስከበር የተጣለባቸውን ታሪካዊ አደራ በብቃት ለመወጣት ማናቸውንም ዓይነት መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት አለባቸው ብለዋል።


ርዕሰ መስተዳደሩ ወጣቶች ማህበራዊ የትስስር ገፆችን  በመጠቀም ህብረተሰቡን በማንቃትና በአንድነት ለአንድ ዓላማ  በማሰለፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ እርስ በራሳችን ተቀራርበንና ተናበን መስራት ይኖርብናል ሲሉም አስታውቀዋል።


ከውይይቱ ተሳታፊዎች  መካከል ወጣት ኢብራሂም መሀመድ በሰጠው አስተያየት፤ ወያኔ በእብሪት ተሞልቶ ምንም በማያውቁ ንጽህ የአፋር አርብቶ አደሮች ላይ በከፈተው ጦርነት ህጻናትና ሴቶች አዛውንቶች ሳይቀሩ ማጥቃቱን ተናግሯል። 


የጥፋት ቡድኑን ለማስወገድ መንግስት የሚሰጠውን  ስምሪትን  በመቀበል  ማናቸውንም  መስዋዕትነት ለመከፈል ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

ወጣት መሐመድ አሊ በበኩሉ ፤ ዛሬ ጁንታው በአፋር ህዝብ ላይ የፈጸመው የግፍ ወረራ ታላቁን ትግራይ ለመመስረት በሌሎች አካባቢዎች ሞክሮ ሲያቅተው  የመጨረሻም አማራጩ አድርጎ የወሰደው ፋሺስታዊ ተግባር መሆኑን ተናገሯል።

ቡድኑ አሁን እየፈጸመ ያለው ግፍ ባለፉት 27 ዓመታት አፋርን ጨምሮ በሌሎችም የሀገሪቱ አካባቢዎች  ዘርፎ ባጠራቀመው ሃብት መሆኑ  የጭካኔው  ጥግ የሚያሳይ ተጨባጭ ሃቅ ነው ብሏል።
የአፋር ህዝብ በታሪክ እንደሚታወቀው ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን  የሀገሩን ዳር ድንበር በማስጠበቅ በተለያዩ ጊዜያት  የመጡ የውጭ ወረራዎችን በመመከት  ሀገራዊ አንድነቱን ሲጠብቅ የቆየ መሆኑን ወጣት መሐመድ አስታውሷል።

ወያኔ በህዝባችን ላይ ያወጀውን ወረራ የመቀልበስ ታሪካዊ አደራ በእኛ ወጣቶች ላይ የወደቀ ወሳኝ ሃላፊነት በመሆኑ ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻችንን ለመወጣት ቁርጠኛ ነን ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም