ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍና ስንቅ ማዘጋጀት እንደቀጠለ ነው

95

ለአገር መከላከያ ሰራዊትና ከየክልሎች ለተውጣጡ ልዩ ሀይሎች ድጋፍና ስንቅ ማዘጋጀት እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነው።

በዚህም በአዲስ አበባ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ሴቶች አደረጃጀት አባላት ለአገር መከላከያ ሠራዊት ስንቅ በማዘጋጀት ያላቸውን ድጋፍ ካሳዩ እናቶች ናቸው።

ከአባላቶቻቸው ጋር ስንቅ ሲያዘጋጁ የተገኙ እናቶች መካከል  ወይዘሮ ውዴ መንግስት አንዷ ናቸው። ወይዘሮ ውዴ መንግስት  በአዲስ አበባ አቃቂ ክፍለ ከተማ ሴቶች አደረጃጀት አባል ሲሆኑ  ዛሬ ለመከላከያ ሰራዊት ስንቅ እያዘጋጁ መሆናቸውን ይናገራሉ። “ለመከላከያ ሰራዊት ደጀን ለመሆን እንሰራለን ያሉት ወይዘሮ ውዴ”፤ ለዚህም ስንቅ ለማዘጋጀት ሴቶች ተሰብሰብናል ሲሉም ይገልጻሉ።

በዛሬው ዕለት በስንቅ ዝግጅቱ የተሳተፉት ሴቶች የአገር መከላከያ ሠራዊቱን ለመደገፍ ጦር ግንባር ድረስ ለመሄድ ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል።

ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን በአገሪቷ ላይ የደቀነው አደጋ እስከሚቀረፍ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

ለሠራዊቱ የሚያስፈልገውን ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ጭምር ዝግጁ እንደሆኑም ተናግረዋል።

ተግባሩ ቢያንስ እንኳን እዚህ የተገኘነው አለንልህ ከጎናችሁ ነን ለማለት ነው ያለችው ደግሞ ስንቅ በማዘጋጀት ላይ የነበረችው ወይዘሮ በእናትላይ ተረፈ ናቸው። የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዐላማ ለብሳ በስሜት የምትናገረው ይቺው እናት “ለመከላከያ ሰራዊታችን ስንቅ ማዘጋጀት ከዜግነት ግዴታችን ጥቂቱ ነው” ሲሉ ለጀግናው ያላቸውን ክብርና ድጋፍ ይገልጻሉ።

ሌላኛዋ እናት ወይዘሮ ኤልሳ ጌታቸው በበኩላቸው መከላከያው ከጀርባው የተወጋው የሚያሳዝነው እኛው በእኛው መሆኑን ገልጸው፤ “የውስጥ አይጥ ነው ያደረገው፤ እኛ ኢትዮጵያዊያን በፍቅር በአንድነት የምንኖር ህዝቦች ነን” ሲሉ በቁጭት ይናገራሉ።

የክፍለ ከተማው ሴቶች ማኅበር ሊቀመንበር ወይዘሮ ወርቅነሽ ዘነበ በበኩላቸው በአገር ላይ የተጋረጠውን አደጋ በጋራ ለመከላከል ባላቸው አቅም ከሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን ለማሳየት የስንቅ ዝግጅት ማድረጋቸውን ያብራራሉ።

በክፍለ ከተማው በሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች የስንቅ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ፈቲያ መሐመድ ናቸው።

ወይዘሮ ፈትያ አክለውም በክፍለ ከተማው በዛሬው እለት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ስንቅ እየተዘጋጀ መሆኑን ይገልጻሉ። ባለፈው ዓመት የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የክፍለ ከተማው ሕዝብ ከ100 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉንም በማስታወስ።

ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን ሠላም እንዳይኖር እኛ ካልመራን አገሪቷን እናበጣብጣለን በማለት ተግቶ እየሰራ መሆኑን የሚገልጹት ዋና ስራ አስፈጻሚዋ፤ በዚህም  የክፍለ ከተማው ነዋሪ ለሠራዊቱ ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ የአካባቢወን ሠላም የመጠበቅ ስራውንም እንዲያጠናክር አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም