የአሸንዳ በዓል ሰላምና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል ፡-የትግራይ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

247
መቀሌ ነሀሴ 2/2010 የአሸንዳ በዓል ሰላምና አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በድምቀት ለማክበር መዘጋጀቱን ቢሮው አስታውቋል፡፡ የአሸንዳን በዓል አከባር ዝግጅት አስመልክቶ  ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መግለጫም ሰጥቷል፡፡ በእዚህ ወቅት እንደተገለጸው በየዓመቱ ነሀሴ 15 ቀን የሚከበረው የአሸንደ በዓል ዘንድሮ "አሸንዳ ለሰላምና ለአንድነት" በሚል መሪ ቃል በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል። የቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ዘነቡ ሀለፎም እንዳሉት የአሸንዳን በዓል በካርኒቫል መልክ ለማክበር ሲደረግ የነበረው የዝግጅት ሥራ ተጠናቋል፡፡ እንደ ወይዘሮ ዘነቡ ገለጻ ከበዓሉ በፊት ባሉት ቀናት የአሸንዳ በዓል ታሪካዊ አመጣጥና ባህላዊ እሴቶችን የሚገልጽ የፓናል ውይይት ይካሄዳል፡፡ የአሸንዳ በዓል ከክልሉ አልፎ የሌሎች የአገሪቱ ህዝቦች ሀብት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸው፣ ባህላዊና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ ለትውለድ ለማስተላለፍ በበዓሉ ላይ አውደ ርዕይ እንደሚዘጋጅም ተናግረዋል፡፡ "ልጃገረዶች የየአካባቢያቸውን ባህል ከማንጸባረቅ ባለፈ በወላጆቻቸው ባህላዊ አለባበስ አጊጠው የአሸንዳን በዓል ሊያደምቁ ይገባል" ያሉት ደግሞ የክልሉ ሴቶች ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር የትምወርቅ ገብረመስቀል ናቸው። ዶክተር የትምወርቅ እንዳሉት በክልሉ የሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በአሸንዳ በዓሉ ላይ ታድመው የአገራቸውን ባህል እንዲያነጸባርቁ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ ይህም የሁለቱን አገራት ህዝቦች ወንድማዊ ትስስርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የቢሮ ኃላፊዋ አመልክተዋል፡፡ የአሸንዳ በዓል ልጃገረዶች ሙሉ ነጻነታቸው ጎልቶ የሚወጣበት በዓል መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሴቶች ማህበር ተወካይ ወይዘሮ ርግበ አብርሀ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ርግበ እንዳሉት ህብረተሰቡ ባህሉን የሚበርዙ ተግባራትን መከላከልና በዓሉን ለማክበር ወደ አደባባባይ የሚመጡ ልጆችም ሥርአቱን ጠብቀው በዓሉን እንዲያከብሩ መምክር ይኖርበታል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም