የሕዳሴው ግድብ የውሃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን ሲያሰራጩት የነበረውን ሀሰተኛ መረጃ ያጋለጠ ነው - ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ

129

ሀምሌ 17/2013 ( ኢዜአ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን ጉዳት ያደርስብናል በማለት ሲያሰራጩ የነበረውን የሀሰት መረጃ እንዳጋለጠ የዓረብ አገራት ግንኙነት ተመራማሪ ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ ገለጹ።

የግድቡ ውሃ ሙሌት በታችኛው ተፋሰስ አገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ ማሳያም ነው ብለዋል።

የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት መገባደዱን በተያዘው ሳምንት መግለጻቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያና የዓረብ አገራት ግንኙነት ተመራማሪ ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ የግድቡ ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን በሙሌቱ ምክንያት የውሃ እጥረት ያጋጥመናል ብለው ሲያሰራጩት የነበረውን የሀሰት መረጃ ያጋለጠ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ሙሌቱ ሁለቱ አገራት የግድቡን ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግ እንዳይሞላ ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት ፍሬ አልባ ያደረገ እንደሆነም ተናግረዋል።

የውሃ ሙሌቱ የተከናወነው እ.አ.አ 2015 ሶስቱ አገራት በሱዳን ካርቱም በፈረሙት የመርሆዎች ስምምነት አማካኝነት ነው ብለዋል።

"ኢትዮጵያ ሙሌቱን ያደረገችው በጥንቃቄና የታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ላሉባቸው ስጋቶች ምላሽ በሰጠ መልኩ ነው፤ ዓለም ሙሌቱ የተሳካ እንደነበር ለማየት ችሏል" ሲሉ ነው አል-ሀሪሪ የገለጹት።

እስካሁን የተከናወኑ የግድቡ ስራዎች ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ማንም ላይ ጉልህ ጉዳት ለማድረስ ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላት እንዲረዱት ያስችላቸዋል ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ በተጨማሪ ሁለት የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩ ተርባይኖች ማንቀሳቀስ የሚያስችል የውሃ መጠን መያዝ መቻሉን የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ገልጸው ነበር።

ሁለቱ ተርባይኖች በወራት ጊዜ ውስጥ ሃይል እንደሚያመነጩ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ተናግረዋል።

ተርባይኖቹ ኤሌክትሪክ እንዲያመነጩ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ስራ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ትልቅ የሚባል ስኬት እንደሆነ ነው ዛይድ ዜዳን አል-ሀሪሪ የሚገልጹት።

በተጨማሪም ሙሌቱና የተርባይኖቹ ስራ መጀመር ሕዝቡ በመንግስት ላይ ያለውን እምነት እንዲጨምር እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

የሕዳሴ ግድብ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለግብጽና ለሱዳን እንዲሁም ለቀጣናው ጥቅም የሚሰጥ እንደሆነም አመልክተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሁለተኛው ዙር የውሃ ሙሌት ግብጽና ሱዳን የአቋም ለውጥ አሳይተው ወደ ድርድር እንዲመጡ ሊያደርጋቸው እንደሚችልም ነው አል-ሀሪሪ ግምታቸውን ያስቀመጡት።

በአጠቃላይ በታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተመዘገቡ ስኬቶች ግብጽና ሱዳን እንዲሁም አጋሮቻቸው የኢትዮጵያን ፍላጎትና አቋም አስመልክተው የሚያሰራጩትን የተዛባና የተሳሳተ መረጃ እንዲስተካክሉ እንደሚያያደርግ አክለዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠቃላይ አፈጻጸም ከ80 በመቶ በላይ መድረሱ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም