የትምህርት ስርዓቱ ለሀገራዊ እድገት ፋይዳ እንዲኖረው በትኩረት ይሰራል ---የትምህርት ሚኒስቴር

118

አዳማ (ኢዜአ) ሐምሌ 16/2013 የትምህርት ስርዓቱ ሀገሪቷን ከድህነትና ኋላቀርነት ማላቀቅ እንዲችል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ጥራት ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴሩ በትምህርት ጥራት ላይ በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ካሉ የትምህርት ቢሮ አመራሮች፣ የሥራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር ዛሬ በአዳማ ከተማ እየመከረ ነው።

የትምህርት ሚንስቴር ዴኤታ ዶክተር ገረመው ሁሉቃ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት የትምህርት ስርዓቱ ሀገሪቱን ከድህነትና ኋላቀርነት ማላቀቅ በሚችልበት መልኩ ሊተገበር ይገባል።

ለተግባራዊነቱ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትን ጥራት ማስጠበቅ እንደሚገባ ያመለከቱት ዶክተር ገረመው  በአሁኑ ወቅት በተለይ የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች መሰረታዊ ዕውቀት እየጨበጡ እንዳልሆነ ተናግረዋል

በሀገሪቱ ከ50 ሺህ በላይ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም ተማሪዎቹ በአግባቡ ማንበብና መፃፍ እየቻሉ እንዳልሆነ አመልክተዋል።

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን መሰረታዊ ዕውቀትና ክህሎት ይዘው እንዲወጡ ማስቻል አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ዶክተር ገረመው አስገንዝበዋል።

የትምህርት ቤት አመራሮች በተለይ ርዕሰ መምህራንና ምክትል ርዕሰ መምህራን በአቅም ግንባታ፣ በአመለካከትና በተግባር ለውጥ ላይ አተኩረው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

አጋሮች የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉት የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ተማሪዎች ተገቢውን ዕውቀት እንዲጨብጡ ለማስቻል መሆኑን አመልክተዋል።

"አሁን ባለው ሁኔታ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ሰፊ ክፍተት ይታያል" ያሉት ዶክተር ገረመው ክፍተቱን  ለመቅረፍ በአራት ክልሎችና አንድ የከተማ አስተዳድር ላይ ተማሪዎችን መሰረታዊ ዕውቀት የማስጨበጥ  የሙከራ ፕሮጀክት መተግበሩን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ በተያዘው በጀት ዓመት በሁሉም ክልሎች እንደሚተገበር አስታውቀዋል።

ዶክተር ገረመው እንዳሉት ፕሮጀክቱ የርዕሰ መምህራንን የመፈፀምና የማስፈፀም አቅም ግንባታ እንዲሁም በመምህራን የትምህርት አሰጣጥ ዘዴ ላይ ያተኩራል።

በተጨማሪም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት፣ የልጃገረዶችና አካል ጉዳተኞች የትምህርት ተሳትፎ ላይ እንደሚያተኩር  አመልክተዋል።


"በመፈጸም አቅም ግንባታ፣ በዕውቀትና ክህሎት፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሳደግ እንዲሁም በጥናትና ምርምሮች ላይ በትኩረት እንዲሰራ ቴክኒካዊ ድጋፍ እያደረግን ነው" ያሉት ደግሞ የ"ታርጌት ኢትዮጵያ" ግብረሰናይ ድርጅት የተቀናጀ ቴክኒካዊ ድጋፍ ቡድን መሪ ዶክተር አብዱ ዘለቀ ናቸው።

በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ ያለው ፕሮጀክት ሙሉ በሙሉ ውጤታማ እንዲሆን በቴክኒክና በጥናትና ምርምር ድርጅቱ እገዛ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የእንግሊዝ ኤምባሲ የኢንግሊዝ ተራድዖ ድርጅት ተወካይ ወይዘሮ ሰዊት ደስታ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ ለትምህርት የደረሱ ህፃናት፣ አካል ጉዳተኞችና ሴቶች በትምህርት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

"በገጠራማ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሴቶችና የአካል ጉዳተኞች የትምህርት ተሳትፎ አሁንም አነሰተኛና በሚፈለገው መልኩ አይደለም" ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ ለሦስት ዓመታት እንደሚቆይና ለማስፈፀሚያ የሚሆን ከ19 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ከእንግሊዝ ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ መገኘቱን ገልጸዋል።

"የልጃገረዶች የትምህርት ተሳትፎን ለማጠናከር፣ የርዕሰ መምህራን አቅም ለማጎልበት፣ የሴት ተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ ለመቀነስና የትምህርት ተሳትፎን ለማሳደግ ይሰራል" ብለዋል።

በተጨማሪም ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህፃናት የትምህርት ዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንደሚውል ወይዘሮ ሰዊት አስታውቀዋል።

በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው መድረክ ከሁሉም ክልሎች የተወጣጡ ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ  የትምህርት ዘርፉ አጋሮች በበይነ መረብ በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም