ግምታቸው 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተያዙ

84

ነገሌ፣ ሀምሌ 16/2013/ኢዜአ/ በጉጂ ዞን ሶስት ወረዳዎች በተደረገ ድንገተኛ አሰሳ ከውጭ ሀገር በህገ ወጥ መንገድ ገብተው የተከማቹ ግምታቸው 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የኮንትሮባንድ እቃዎች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹ የተያዙት በዞኑ ሻኪሶ፣ አጋ ዋዩና ሊበን ወረዳዎች ከሀምሌ 5 እስከ 13 ቀን 2013 ዓም በተደረገ አሰሳ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኮማንደር ብዙነህ ቦደና ለኢዜአ አስታውቀዋል።

ከተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል 208 ቦንዳ ልባሽ ጨርቅና ጫማዎች፣ ባለ 24 ኢንች 18 ከለር ቴሌቭዥኖች፣ 599 የተንሳቃሽ የእጅ ስልክ ቀፎዎችና አንድ ባለሶስት እግር ባጃጅ ተሽከርካሪ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

በወረዳዎቹ ህዝብ ትብብርና ጥቆማ በዞኑ ፖሊስ የተያዙት የኮንትሮባንድ እቃዎች 5 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ  ግምት እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

የኮንትሮባንድ እቃዎቹን በማዘዋወርና በማከማቸት ከተጠረጠሩ ግለሰቦች መካከል ፖሊስ እስካሁን አራቱን በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳያቸውን እያጣራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በህገ ወጥ ተግባሩ ተሰማርተው ለጊዜው የተሰወሩ ተጠርጣሪ ግለሰቦችን ፖሊስ ከዞኑ ህዝብ ጋር በመተባበር አድኖ ለመያዝ ክትትል በማድረግ ላይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በህገ ወጥ መንገድ ተከማችቶ በፖሊስ የተያዘው የኮንትሮባንድ እቃ በሞያሌ ገቢዎችና ጉምሩክ ነገሌ ቅርንጫፍ ገቢ መደረጉን አስታውቀዋል።

"ፖሊስ ከዞኑ ህዝብ ጋር በመተባበር የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ለመከላከል የጀመረው  የክትትልና ቁጥጥር ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል" ብለዋል፡፡

ህገ ወጥነትን ለመከላከል ሁሉንም ባለድርሻ በማሳተፍ በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የሚመራው የዞኑ ጸረ ኮንትሮባንድ ግብረ ሀይል የድርሻውን እየተወጣ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በኮንትሮባንድ ንግድ ፍትሀዊ የንግድ ውድድርን ለማዛባት የሚሰሩ ህገ ወጦችን ለመከላከል የዞኑ ህዝብ እየሰጠ ያለው ጥቆማ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም