ከተራሮችና ወንዞች ንጽህ ውሃ ብቻ እንዲወርድ ተፋሰሶችን አረንጓዴ የማልበሱ ሥራ ማጠናከር ይገባል---ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ

86

ባህር ዳር ሐምሌ 15/2013 (ኢዜአ) ከተራሮችና ወንዞች ንጽህ ውሃ ብቻ እንዲወርድ ተፋሰሶችን አረንጓዴ ለማልበስ የተጀመረው የችግኝ ተከላ ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ አሳሰቡ።

ሶስተኛው ዙር የአንድ ጀምበር የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ  መረሃ ግብር ዛሬ በባህር ዳር ቤዛዊት ተራራ ላይ ሲጀመር ዶክተር ፋንታ እንዳሉት፤ በአረንጓዴ አሻራ የሚተከሉ ችግኞችን ህብረተሰቡ በባለቤትነት መንከባከብ ይኖርበታል።

"በራሳችን አቅም እየገነባን ያለነው ታላቁ የኢትዮጵ የሕዳሴ ግድብ ለስኬት እንዳይበቃ የሚታትሩ ጠላቶቻችንን በመመከት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማውረስ ችግኝ ተከላው መጠናከር አለበት " ብለዋል።

ከተራቆቱ ተራሮችና ወንዞች  ንፁህ ውሃ እንዲወርዱ የተጀመረው በአረንጓዴ የማልበስ ሥራን ህብረተሰብ አጠናክሮ ሊቀጠል እንደሚገባ  አሳስበዋል።

"በሀገሪቱ ላይ የተጋረጠውን የህልውና ዘመቻ ከመጋፈጥ ጎን ለጎን የልማት ስራዎቻችን ተጠናክረው ይቀጥላሉ" ያሉት ድግሞ የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መለስ መኮንን ናቸው።

በህልውና ዘመቻው የጸጥታ አካላት መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆናቸው ጠቅሰው፣ "እኛም ለአንድ ደቂቃ ሳንዘናጋ የግብርና ስራችንን እያከናወንን እንገኛለን" ሲሉ ገልጸዋል።

በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራና መደበኛው  መርሃ ግብር በክልሉ በ185 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ 2 ቢሊዮን ችግኝ ለመትካል ታቅዶ እየተሰራ  መሆኑንም አስረድተዋል።

ዶክተር መለስ እንዳሉት፤ ከሚተከለው ችግኝ  248 ሚሊዮን ዛሬ በአንድ ጀምበር  ለመትከል ከታቀደው በላይ ማከናወን መቻሉን  አስታውቀዋል።

በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ የተገኘው አርቲስት ስለስሺ ደምሴ /ጋሽ አበራ ሞላ/ በበኩሉ  በዓባይ ገባር ወንዞች ስር በሚገኙ ተፋሰሶች የችግኝ ተከላ ሥራው መጠናከር እንዳለበት ተናግሯል።

"የህዳሴውን ግድብ ከደለል በመጠበቅ ለበዙ ዓመታት ለመጠቀም የችግኝ ተከላ ስራውን በስፋት ማከናወን፣ ችግኞችን መንከባከብና መጠበቅ ከሁለም ዜጋ ይጠበቃል" ብሏል።

ተከላው የተሳተፉት የጣና ሐይቅና ሌሎች የውሃ አካላት ጥበቃና ልማት ኢጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አያሌው ወንዴ እንዳሉት፤ ችግኝን ከመትከል ባለፈ በባለቤትነት ተንከባክቦ ማሳደግ ይገባል።

የጣና ሐይቅ እና የህዳሴውን ግድብ ከደለል ለመጠበቅ በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ ያለው የችግኝ ተከላ ለታችኛው ተፋሰስ ያለውን አንድምታ በቀጣይ በጥናት አስደግፎ ለማሳየት እንደሚያስችልም ገልጸዋል።

 ባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት በክልሉ በተካሄደ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከተተከለው 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን የሚጠጋ ችግኝ ውስጥ  78 በመቶው መጽደቁ ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም