ሰብዓዊ ድጋፍ ለዜጎች እንዳይደርስ ማስተጓጎል የሞራል ውድቀትን አመላካች ነው - የሰብዓዊ መብትና ህግ ባለሙያዎች

112

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 15/2013 ( ኢዜአ) የሰብዓዊ ድጋፍን ማስተጓጎል ንጹሃን ዜጎችን ለበለጠ ጉዳት ከመዳረግ ባሻገር የሞራል ውድቀትን እንደሚያሳይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ሰብዓዊ መብትና የህግ ባለሙያዎች ገለጹ።

መንግስት በትግራይ ክልል ሰብዓዊ ድጋፍን በተገቢው መልኩ እንዲዳረስና አርሶአደሩ የመኸር እርሻን ያለምንም ስጋት እንዲያከናውን የተናጥል ተኩስ ማቆም ማወጁ ይታወሳል።

ይሁንና ወደ ክልሉ የሚላከው የሰብዓዊ ድጋፍ በአፋር በኩል ወደ መቀሌ ሲጓጓዝ የአሸባሪው የህወሃት ቡድን መንገዶችን በከባድ መሳሪያ በመደብደብ ድጋፉን ማስተጓጎሉን የአደጋ ስጋትና ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር በስልክ ቆይታ ያደረጉት ሰብዓዊ መብትና የህግ ባለሙያዎች እንደገለጹት፤ በዓለምአቀፍ የጦርነት ህግ መሰረት ሁለት ተፋላሚ ኃይሎች ንጹሃንን ዒላማ እንዳይሆኑ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።

በተለይም በግጭቱ ምክንያት ንጹሃን ዜጎች ለረሃብ እንዳይጋለጡና የሰብዓዊ መብት ጥሰት እንዳይደርስባቸው ተፋላሚ ኃይሎቹ ከፍተኛ ኃላፊነት እንዳለባቸውም ነው የገለጹት።

ከዚህ አኳያ የሽብር ቡድኑ ወደ ትግራይ ክልል የሚሄደውን ድጋፍ ለዜጎች በአግባቡ እንዳይደርስ ያደረገው ማስተጎጎል "በክልሉ የሰብዓዊ ቀውስ እንዲፈጠር ያደርጋል" ነው ያሉት።

ይህ አይነቱ ድርጊት ንጹሃን ዜጎችን ለበለጠ ጉዳት ከመዳረግ ባሻገር የሞራል ውድቀትን እንደሚያሳይም ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት ዳይሬክተርና የህግ ባለሙያ መስሁድ ገበየሁ የሰብዓዊ ድጋፍን ማስተጓጎል በምንም መልኩ ተቀባይነት እንደሌለው ነው ያስረዱት።

በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የህግ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ኩሌ ኩርሻ በበኩላቸው የሰብዓዊ ድጋፍን ማስተጓጎል የዓለም አቀፍ ህግ ጥሰት መሆኑን ነው የገለጹት።

ድርጊቱ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከሚያስከትለው ሰብዓዊ ቀውስ ባሻገር ከፍተኛ የሞራል ውድቀትን አመላካች መሆኑንም ተናግረዋል።

ድርጊቱ በሰብዓዊ ፍጡር ላይ ከሚፈጸም ወንጀል ጋር እንደሚያያዝም ነው ያብራሩት።

ወደ ትግራይ ክልል የሚጓጓዝ ሰብዓዊ ድጋፍ በአግባቡ ተፈትሾ በአፋጣኝ ተደራሽ እንዲሆን መንግስት ተጨማሪ የፍተሻ ማሽኖች ተከላ እያደረገ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።

ይሁንና አሸባሪው ህወሃት ቡድን “ወደ ትግራይ የሚሄድ እርዳታ አይኖርም” በማለት የአፋር ክልል ዞን አራት ሰርዶ ኬላ አካባቢን በከባድ መሰሪያ በመደብደብ ድጋፉን ማስተጓጎሉን ከአካባቢ የተገኙ ምንጮች ለኢዜአ ገልጸዋል።

በዚህም ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን የጫኑ 60 ተሽከርካሪዎች ወደ ትግራይ ክልል የሚያደርጉት ጉዞ አስተጓጉሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም