የክልሉ አመራሮች የሕግ የበላይነት ማስከበር ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው---ምክትል ፕሬዝዳንት ጠይባ ሐሰን

93
አዲስ አበባ ነሓሴ 2/2010 የአሮሚያ ክልል ከፍተኛ አመራሮች በሚሰሩበት አካበቢ የሕግ የበላይነት እንዲከበር ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን አሳሰቡ። የኦሮሞ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ሥራዎች ላይ ትናንት ውይይት ባደረጉበት ወቅት ወይዘሮ ጠይባ እንዳሉት አሁኑ ወቅት በክልሉ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ የሁሉም አካላት የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑ ለውጡን ለማስቀጠል አመራሩ የሕግ የበላይነት ማስከበር ላይ ማተኮር አለበት። በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለማስወገድ የፖለቲካ አመራሩ ከየትኛውም ጊዜ በተሻለ ሁኔታ በቁርጠኝነት ሥራውን ማከናወን እንዳለበት ገልጸዋል። ከፍተኛ አመራሮቹ ወደ ሥራቸው ሲመለሱ ማከናወን ከሚገባቸው ተግባራት መካከል የሕግ የበላይነትን ማስከበር ላይ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ወይዘሮ ጠይባ አሳስበዋል። እንዲሁም ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን ከሚመለከተው ጋር ተቀራርበው መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመው ከሁሉም በላይ የልማት ሥራዎችን ማስቀደም ይገባል ብለዋል። መንግሥት የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ መወጣት እንዲችልና  ሕዝቡ ሰላማዊ ኑሮውን እንዲመራ አመራሩ ንቁ መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል። እንደ ወይዘሮ ጠይባ ገለጻ ከፍተኛ አመራሮቹ የአገር ሽማግሌዎችን፣ የሐይማኖት አባቶችን እና የተለያዩ የኀብረተስብ ክፍሎችን ያሳተፈ ሥራ መስራት እንደሚገባም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት በላይኛው የአመራር እርከን ላይ የተገኘውን ለውጥ ዘላቂ ነው ብሎ ከማሰብ ይልቅ ቀጣይነት ባለው መልኩ ፊት ለፊት ወጥቶ መታገልና የሚፈለገውን ግብ ማሳካትም የአመራሮቹ ግዴታ መሆኑን አስረድተዋል። ከሁሉም በላይ የፖለቲካ አመራሩ በክልሉ እያጋጠሙ ያሉ ወቅታዊ ችግሮችን ለመፍታት ፖለቲካዊ ትርጉም ሰጥቶ የመተንተንና መፍትሔ የማበጀት ሥራም ከኃላፊዎች የሚጠበቅ ጉዳይ ነው ብለዋል። የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አሁን የደረሰበትን የትግል ምዕራፍ የሚያመላከት ስያሜና መለያ በማስፈለጉም ስያሜውን ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀይር እንደሆነ ድርጅቱ መግለጹ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም