በሐረሪ ክልል ኮሮናን ለመከላከል የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት እውቅና ተሰጠ

78

ሐረር ፤ ሐምሌ 15/ 2013(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል የኮሮና ወረርሽኝ ለመከላከል በተካሄደው እንቅስቃሴ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የጤና ባለሙያዎች ፣ ሰራተኞች እና የተለያዩ ተቋማት ዛሬ እውቅና ተሰጠ።

በእውቅና አሰጣጥ መድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንደገለጹት፤ በክልሉ የኮሮና ቫይረስ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ  ጠንካራ የመከላከል ስራ ተከናውኗል።


ቫይረሱን በመከላከል  ሂደት የሌሎችን ህይወት ለማዳን መስዋዕትነት ለከፈሉ የጤና ባለሙያዎች ሁሌም ሲዘከሩ ይኖራሉ ብለዋል።


በክልሉ በአሁኑ ወቅት ቫይረሱን ከመከላከል አንፃር አቅም ማጎልበት ተችሏል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም ሆኖ አሁንም ባለመዘናጋት የጥንቃቄ ዘዴዎች መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።


የክልሉ መንግስትም የጤና ባለሙያዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች አሁንም ቢሆን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነው ብለዋል።


የጤና ቢሮው  ሀላፊ አቶ ኢብሳ ኢብራሂም በበኩላቸው፤  በክልሉ እስካሁን በቫይረሱ ከተያዙ 4ሺህ 445 ሰዎች ውስጥ የ177 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስታውሰዋል።


ህብረተሰቡ አሁንም ቫይረሱን ከመከላከል አኳያ የሚያደርገውን ጥንቃቄ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።


የተሰጠው እውቅና በተለይም የጤና ባለሙያዎች እና ሰራተኞች በላቀ ተነሳሽነት ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ እንደሚያነሳሳ ገልጸዋል።


ኮሮናን ለመከላከል የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ  የተለያዩ ተቋማት ጨምሮ  የእውቅና ምስክር ወረቀት ከዕለቱ የክብር እንግዶች ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም