በተሽከርካሪ ስርቆት የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች እስከ 13 አመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ

71

ፍቼ፣ ሀምሌ 15/2013/ኢዜኣ/ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የውጫሌ ወረዳ በተሽከርካሪ ስርቆት የተከሰሱ ሁለት ግለሰቦች እስከ 13 አመት በሚደርስ እስራት ተቀጡ።

ፍርድ ቤቱ የቅጣት ውሳኔውን ያሳለፈው በወረዳው ጎርፎ ቀበሌ ነዋሪ በሆኑ ባይልኝ ፍቅሬና ታደለ ወሌ በተባሉ ግለሰቦች ላይ ነው።

የውጫሌ ወረዳ ፍርድ ቤት መሃል ዳኛ አቶ ዳንኤል ቦደና ለኢዜአ እንደገለጹት ግለሰቦቹ  ሰኔ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከለሊቱ 7:00  ሰዓት ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ A3- 65386 አ.አ  የሆነ አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ በመስረቅ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል።

ግለሰቦቹ  57 ኩንታል ጤፍ ጭኖ ከወረ ጃርሶ ወረዳ ቱሉ ሚልኪ ከተማ ወደ አዲስ አበባ  በመጓዝ ላይ የነበረና በድንገት ቆሞ ያገኙትን ተሽከርካሪ ሰርቀው በመሰወራቸው መከሰሳቸውን አመልክተዋል ።

መሀል ዳኛው የግለሰቦቹን የክስ ሁኔታ ሲያስረዱም፣ በእለቱ  የጭነት አይሱዙ አሽከርካሪውና ረዳቱ በጉዞ ላይ እንዳሉ ከመንገድ ዳር ከሚገኝ የጎርፎ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ለመሳለም የተሽከርካሪውን ሞተር ሳያጠፉ አቁመው ይወርዳሉ።

አሽከርካሪውና ረዳቱ በቤተክርስትያኑ ቅጥር ጊቢ ጎራ በማለት ተሳልመው እስኪመለሱ ባለው ቅጽበት ተከሳሾች የቆመውን ተሽከርካሪ አስነስተው እስከ ጭነቱ ይዘው ይሰወራሉ።

ተከሳሾች የሰረቁትን ተሽከርካሪ ሰሌዳ ቀይረው ለጥቂት ቀናት ሲጠቀሙበት ከቆዩ በኋላ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን እንሳሮ ወረዳ ወበሪ ቀበሌ በፖሊስ ክትትል ተይዘዋል ።

ግለሰቦቹ በተከሰሱበት ወንጀል በቀረበባቸው የአቃቤ ህግና የሰው ማስረጃ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው ፍርድ ቤቱ ትላንት በዋለው ችሎት የቅጣት ውሳኔውን አስተላልፏል።

በዚሁ መሰረት ፍርድ ቤቱ አንደኛ ተከሳሽ ባይልኝ ፍቅሬ በ13 ዓመት እንዲሁም ሁለተኛ ተከሳሽ ታደለ ወሌ በ12 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ወስኗል።

ፍርድ ቤቱ የተከሳሾቹን ይግባኝ የማለት መብት እንደሚፈቅድ በችሎቱ መመልከቱን አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም