በኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈመ ዝርፊያና ጥቃት ከ47 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙ ተመለከተ

61

ባህር ዳር ሐምሌ 15/2013 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው 2013 በጀት አመት በኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ በተፈጸመ ዝርፊያና ጥቃት ከ47 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት መውደሙን የአማራ ክልል የኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

በሌላ በኩል በክልሉ በበጀት አመቱ 97 የገጠር ከተሞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ መደረጉ ተነግሯል።

የአገልግሎቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ማተቤ ዓለሙ ለኢዜአ እንደገለጹት በኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ መሰረተ ልማቶች ላይ ሃላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች የሚፈጸም ስርቆትና ጥቃት እየጨመረ ነው።

በተጠናቀቀው የ2013 በጀት ዓመት ከደብረ ማርቆስ ፍኖተ ሰላም፣ ከባህር ዳር ዳንግላ፣ ከጭስ ዓባይ ባህር ዳርና ከአዘዞ ጎንደር ጨምሮ በሌሎች አካባቢዎች በተዘረጉ የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ ስርቆትና ጥቃት  መፈፀሙን ተናግረዋል።

በአካባቢዎቹ ሀላፊነት በማይሰማቸው ግለሰቦች 66 ሺህ ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ተፈተው መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

ተፈተው በተወሰዱ የብረት ምሰሶዎች ምትክ በተቀየሩ የእንጨት ምሰሶዎች ላይም በመጋዝ ቆርጦ የመጣል ሆን ተብሎ የተካሄደ ጥቃት እንደተፈጸመባቸው አመልከተዋል ።

በበጀት አመቱ በሀይል ተሸካሚ መሰረተ ልማት አውታሮች ላይ በተፈጸመ ስርቆትና ጥቃት 47 ሚሊዮን 675 ሺህ  ግምት ያለው ንብረት መውደሙን አስታውቀዋል ።

በተፈጸመው ስርቆትና ጥቃት ከደረሰው የሀብት ኪሳራ በተጨማሪ በደንበኞች የኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ችግርና መጉላላት መፍጠሩን ተናግረዋል።

የብረት ምሰሶዎችን ወደ እንጨት የመተካቱም ሂደት ዘመናዊነትን ወደ ኋላ የመመለስ አስገዳጅ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ስራ አስኪያጁ እንዳሉት ህብረተሰቡ በየአካባቢው የተዘረጉ የኤሌክትሪክ ሀይል ማስተላለፊያ መስመር መሰረተ ልማቶችን የራሱ ንብረቶች መሆናቸውን አውቆ ከዝርፊያ ሊጠብቃቸው ይገባል።።

በየደረጃው ያሉ የአመራርና የጸጥታ አካላትም ለኤሌክትሪክ መስመሮቹ ተገቢውን ከለላ በመስጠት ሃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በሌላ በኩል በክልሉ በበጀት ዓመቱ ህብረተሰቡን የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ ለማድረግ በተሰራ ሥራ 97 የገጠር ከተሞች አገልግሎቱን እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።

በበጀት አመቱ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ በተካሄዱ የማስፋፊያ፣ የመልሶ ግንባታና የፕሮጀክት ስራዎች የ3ሺህ 851 ኪሎ ሜትር የመካከለኛና ዝቅተኛ የሀይል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ከ1ሺህ 500 በላይ ትራንስፎርመሮች መተከላቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም