የቴክኒክና ሙያ ምዘና ከወሰዱ 671 ሺህ 773 ተፈታኞች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ብቁ መሆናቸው ተገለጸ

62
አዳማ ነሓሴ 2/2010 በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የቴክኒክና ሙያ ምዘና ከወሰዱ 671 ሺህ  773 ተፈታኞች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ብቁ መሆናቸውን የፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ገለጸ፡፡ ሀገር አቀፍ የቴክኒክና ሙያ ዘርፍ የ2010 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸም እና ቀጣይ እቅድ ላይ የሚመከር መድረክ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው። በኤጀንሲው የሙያ ደረጃ ምደባና ብቃት ምዘና ዳይሬክተር ንግስት መላኩ በዚህ ወቅት እንዳሉት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በመደበኛና መደበኛ ባልሆኑ ፕሮግራሞች ለ490 ሺህ 360 ሰልጣኞች የሙያ ብቃት ምዘና ለመስጠት ከታቀደው በላይ ተከናውኗል፡፡ በዚህም በሀገሪቱ የቴክኒክና ሙያ ምዘና የወሰዱ 671 ሺህ 773 ተፈታኞች እንደሆኑ አመልክተው ከመካከላቸውም ብቁ ሆነው የተገኙት 60 በመቶ ያህሉ ናቸው፡፡ ብቁ ሆነው ከተገኙት ውስጥም ከ75 በመቶ በላይ ሴቶች እንደሆኑ ጠቁመዋል። "በሀገሪቱ በሚገኙ የአርሶ አደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ላይ ከተመዘኑት 462 ሺህ አርሶና አርብቶ አደሮች መካከል ከ96 በመቶ በላይ ብቁ ሆነው ተገኝተዋል" ብለዋል ዳይሬክተሯ። ምዘናው ያስፈለገው የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ስልጠና  ዘርፍ ተወዳዳሪ የሆነ፣ ተነሳሽነት ያለው፣ የመፍጠርና የማጎልበት አቅም ያዳበረ የሰው ኃይል ለማፍራት መሆኑን ገልጸዋል። የኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪነትና ምርታማነት የሚያጎለብት በዝቅተኛና መካከለኛ ደረጃ የሰለጠነ ብቁ የሰው ኃይል ለመፍጠር ጭምር ነው። በበጀት ዓመቱ በዘርፍ ካጋጠሙ ተግዳራቶች መካከል የብቃት መመዘኛ ማዕከላት አደረጃጀት በሁሉም ክልሎች ወጥ ያለመሆን፣ በምዘና ተግባራ ስርዓት ላይ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከት መኖሩ ተጠቅሷል። በትምህርት ሚኒስቴር የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሳህለስላሴ ተካ በበኩላቸው ዘርፉ ድህነትን ለመቀነስና እድገትን ለማምጣት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል። ለዚህ አስተዋጽኦ የማበርከት የሰው ኃይል ፍላጎትን መሠረት ያደረገ ጥራት ያለው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና መስጠትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሂደትን ለማጎልበት በየደረጃው እየተሰራ ነው። በዚህ ሂደት የሙያ ብቃት ምዘና ተደራሽነትና ተአማኒነት ከማረጋገጥ አንፃር ልዩ ትኩረት የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል። "መደበኛና አጫጭር ስልጠናዎች ገበያው የሚፈልገው ሊሆን ይገባል" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ሁሉንም ስራ ፈላጊ የሙያ ባለቤት በማድረግ ስራ ውሰጥ ለማሰማራት የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል። በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ የትግባራ ዓመታት ብቃቱ በምዘና የተረጋገጠ የሰው ኃይል በማፍራት ለገበያው ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የፌዴራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ ናቸው፡፡ "እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ዘርፉ የበርካታ ዜጎችን ህይወትና ኑሮ እየቀየረ ይገኛል" ብለዋል፡፡ ከዘርፉ ተልዕኮ ስፋት አንፃር እያደገ የመጣውን የህበረተሰቡን የመልማት  ፍላጎት ለማርካትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ለመመለስ የጋራ ርብርብ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል። የምክክር መድረኩ ዓላማ የዘርፉን የ2010 እቅድ አፈጻጸም ላይ የታዩ ክፍተቶችን ለማስተካከል የሚያግዙ ግብአቶችን በመውሰድ የተያዘው የስራ ዘመን እቅድ በተደረጃ አግባብ ለማሳካት የሚያስችል አቅጣጫ ለማስቀመጥ ነው፡፡ ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው መድረክ  በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የትምህርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላትና ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም