የቁልቢ ገብርኤል ንግሥ በዓል በሰላም እንዲከበር ለማስቻል ዝግጅት ተደርጓል

69

ሐረር፣ ሐምሌ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) በመጪው ሰኞ ሐምሌ 19 ቀን 2013 የሚከበረው ዓመታዊው የቁልቢ ገብርኤል ንግሥ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት መደረጉን የጸጥታ አካላት ገለጹ፡፡

የጸጥታ አካላቱ በዝግጅቱ ዙሪያ ውይይት ባካሄዱበት ወቅት እንደተገለጸው፤ በበዓሉ ከምዕመናን በተጨማሪ ቱሪስቶች፣ አምባሳደሮችና ሌሎችም እንግዶች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊና የጊዜያዊ የጸጥታ ግብረ ሃይል ሰብሳቢ ኮማንደር ናስር አህመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የበዓሉ ሰላማዊነት ተጠብቆ እንዲከበር የተለያዩ የጸጥታ አካላት ተቀናጅተው ከምስራቅ ሸዋ ዞን እስከ ባቢሌ ከተማ ድረስ ዝግጅት አድርገዋል።

ከምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች፣ ድሬዳዋ አስተዳደር፣ ሐረሪ ክልልና ፌዴራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ተቀናጅተው እየሰሩ እንደሆነም ጠቁመዋል።

አካባቢው ዳገት፣ ቁልቁለትና ጠመዝማዛ ስለሚበዛው አሽከርካሪዎች የትራፊክ ህግና ደንብ አክብረው ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ከሐምሌ 17 ጠዋት እስከ ሐምሌ 19 ቀን 2013 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ ድረስ ጨለንቆ እስከ ቀርሳ ድረስ ባሉት ከተሞች ዋና መንገድ ላይ ከባድ ተሽከርካሪ ማለፍ እንደተከለከለ ጠቁመዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች ንብረቶቻቸውን በጥንቃቄ እንዲይዙ መክረው፤ ወንጀልን ለመከላከል ሶስት ጊዜያዊ ፖሊስ ጣቢያዎች መቋቋማቸውን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪ ወንጀለኞችም ሲያዙ ውሳኔ ለመስጠት ዐቃቤ ህግና ጊዜያዊ ፍርድ ቤት እንደተቋቋመም ተናግረዋል።

የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለሙ መርጋ በበኩላቸው ጁንታውና መሰል ተላላኪዎች ችግር እንዳይፈጥሩ የፀጥታ አካሉ ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ምዕመናኑም ሃይማኖቱ የሚፈቅደውንና ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ውጭ ይዘው መንቀሳቀስ እንደሌለባቸው አሳስበዋል።

የሜታ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሪያድ መሐመድ በዓሉ በሰላም ለማክበር ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት መካሄዱን ገልጸዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች የጤና ሚኒስቴር መመሪያን በመከተል የኮሮና መከላከያዎችን መተግበር እንደሚገባቸው ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም