የዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዕቅድ 61 በመቶ መከናወኑ ተገለጸ

129

ሐምሌ 14 ቀን 2013 (ኢዜአ) በዘንድሮው የ3ኛ ዙር 'ኢትዮጵያን እናልብሳት' አገራዊ የችግኝ ተከላ መርሐ ግብር እስካሁን 3 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል የአገራዊ ዕቅዱን 61 በመቶ ማሳካት መቻሉ ተገለጸ።

በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚተከለው 6 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ 75 በመቶው ማለትም 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ችግኝ በዓባይ ተፋስስ እንደሚተከልም ተገልጿል።

የመርሐ ግብሩ ብሔራዊ አስተባባሪ ኮሚቴ 3ኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ዝግጅትና ትግበራን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የኮሚቴው አባል የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ሳኒ ረዲ ግንቦት 10 ቀን 2013 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓቢይ አህመድ በይፋ በተጀመረው የችግኝ ተከላ እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2013 ድረስ 3 ነጥብ 71 ቢሊዮን ችግኝ መትከል እንደተቻለ ገልጸዋል።

የብሔራዊ ኮሚቴው አባል የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው በዓባይ ተፋሰስ የሚካሄደው የዘንድሮው ግኝኝ ተከላ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ከደለል ለመጠበቅ ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

በቀጣይም በአንድ ጀምበር በዓባይ ተፋሰስ ውስጥ ችግኝ የመትከል መርሃ ግብር እንደሚከወን ገልፀው፤ "መቼና ምን ያህል ችግኞች ይተከላሉ የሚለውን ኮሚቴው በቅርቡ ያስታውቃል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከሶስት ዓመት በፊት በጀመረችው የአረንጓዴ አሻራ ዘመቻ በመጀመሪያውና በሁለተኛው መርሃ ግብር 9 ቢሊዮን ችግኝ መትከል ችላለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም