የቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

111
አሶሳ ነሀሴ 1/2010 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ፡፡ ትናንት ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው ሆስፒታሉ ለግንባታው  40 ሚሊዮን ወጪ ተደርጎበታል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የህዝብ ግንኙነት፣ ፕሮቶኮልና ዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ አድማሱ ተክሌ በምርቃው  ወቅት እንደገለጹት የሆስፒታሉ ግንባታ  ከተቀመጠለት የማጠናቀቂያ ጊዜ ዘግይቷል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የግንባታ ተቋራጩ አቅም ማነስ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ ለምን አቅም ለሌለው ተቋራጭ እንደተሰጠ የኢዜአ ሪፖርተር ላነሳላቸው  ጥያቄ በሰጡት ምላሽ " ተቋራጩ ስራውን ሲጀምር የግንባታ አቅም እንዳለው የሚያመላክቱ መረጃዎች ነበሩ"ብለዋል፡፡ 100 የህሙማን መኝታ አልጋዎች ያሉት ሆስፒታሉ የቀዶ ጥገና፣ የተመላላሽ ህክምናና ሌሎችንም አጠቃላይ የጤና  አገልግሎቶችን እንደሚሰጥ ተመልክቷል፡፡ ቡለን ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ፋምብሬ ሌዲ በሰጡት አስተያየት ከዚህ በፊት ለከፍተኛ ህክምና ፍለጋ  ከ300 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዘው ባህር ዳር ከተማ  በመሄድ ለእንግልትና ለተጨማሪ ወጪ ይዳረጉ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የሆስፒታሉ በአቅራቢያቸው መገንባት ይህንን ችግር እንደሚያቃልልላቸው ነው የተናገሩት፡፡ ሌላው የከተማው ነዋሪ አቶ አርባው ቦጋለ በበኩላቸው ሆስፒታሉ በቂ ባለሙያና መድኃኒት ከተሟላለት የነበረባቸውን የጤና አገልግሎት ችግር እንደሚፈታላቸው ገልጸዋል፡፡ ሆስፒታሉን መርቀው የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰንና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በጋራ በመሆን ነው፡፡ የቡለን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከ100 ሺህ ለሚበልጡ የአካባቢው ነዋሪዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችል በምረቃው ወቅት ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም