በኢሉአባቦር ዞን የቅመማ ቅመም ልማትን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው

185
መቱ  ነሀሴ1/2010 በኢሉአባቦር ዞን የቅመማ ቅመም ልማትን ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ቡና፣ ሻይና ቅመማ ቅመም ልማትና ግብይት ባለስልጣን አስታወቀ። የባለስልጣኑ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲሱ ንጉሴ እንደገለጹት በዞኑ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የቅመማ ቅመም ልማትን ለማስፋፋት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው። በእዚህም በየዓመቱ አንድ ሺህ ሄክታር አዲስ መሬት እየለማ ሲሆን ከ5ሺህ የሚበልጡ አዲስ አርሶ አደሮችም የልማቱ ተሳታፊ ሆነዋል። የቅመማ ቅመም ልማትን ለማስፋፋት በሚደረገው ጥረት ዘንድሮ ብቻ በዞኑ 70 ሺህ ችግኞች ለአርሶ አደሩ እንዲሰራጭ መደረጉንም ገልጸዋል። በተጠናቀቀው ሐምሌ ውር የተሰራጩት ችግኞች ከቴፒ የግብርና ምርምር ማዕከል የተገኙና የተሻሻሉ ዝርያዎች መሆናቸውንም ነው አቶ አዲሱ ያስታወቁት ። ከተሰራጩት የቅመማ ቅመም ዝርያዎች መካከል ቁንዶበርሬ፣ ዝንጅብል እርድና ኮረሪማ የሚጠቀሱ ሲሆን ዝርያዎቹ በመቱ እና ቢሎ ኖጳ ወረዳዎች በሚገኙ የመንግስትና በግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ማሳ የተባዙ መሆናቸውን አስረድተዋል። አቶ አዲሱ እንዳሉት በያዮ፣ ዶረኒ እና አልጌ ሳቺ ወረዳዎች በተመሳሳይ ሁኔታ 600 ኩንታል የተሻሻሉ የእርድና የዝንጅብል ዝርያዎች ተመርተው ችግኙ እንዲሰራጭ ተደርጓል። በወረዳዎቹ በልማቱ የተሳተፉ 120 አርሶ አደሮች በተያዘው የክረምት ወቅት ከ150 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የቅመማ ቅመም ዝርያዎቹን እያለሙ መሆናቸውን ገልጸዋል። የተሻሻሉት የቅመማ ቅመም ዝርያዎቹ በሽታን በመቋቋም ከፍተኛ ምርት በመስጠት አርሶ አደሩ ከዚህ ቀደም ለረጅም ዓመታት ሲጠቀምባቸው ከነበሩት የተሻሉ መሆናቸውነም አቶ አዲሱ ተናግረዋል። በተለይ የእርድ ምርታማነትን በሄክታር ከ70 ኩንታል ወደ 125 ኩንታል፣ ኮረሪማን ከ6 ኩንታል ወደ 8 ኩንታል የማሳደግ አቅም እንዳላቸው በማሳያነት ጠቅሰዋል። በቅመማ ቅመም ልማት ሥራ ላይ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች የገበያ ትስስር ለመፍጠር በባለስልጣኑ በኩል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል። በአሌ ወረዳ የገብረዲማ ቀበሌ አርሶ አደር አለማየሁ ሽፈራው በበኩላቸው እንዳሉት በ10 ሄክታር መሬት ላይ ከጫካ ቡና ጋር በጥምረት ኮረሪማ እንደሚያለሙ ተናግረዋል። በዚህ ዓመት ብቻ ካመረቱት 10 ኩንታል እርጥብ ኮረሪማ ምርት ሽያጭ ከ40 ሺህ ብር በላይ ገቢ በማግኘተ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል። በዲዱ ወረዳ ጎርዶሞ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር በፈቃዱ ፈይሳ በበኩላቸው "ከቡና ጋር በጥምር ከማለማው ኮረሪማ በየዓመቱ እስከ 20ሺህ አገኛለሁ" ብለዋል። ካለፉት አራት ዓመታት ወዲህ በግማሽ ሄክታር ማሳቸው ላይ እርድ በማልማት በዓመት 15 ኩንታል ምርት እያገኙ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በመቱ ወረዳ ቡሩሳ ቀበሌ አርሶ አደር ተሰማ ጆቴ ናቸው። በኢሉአባቦር ዞን በ2010/2011 የመኽር እርሻ 7 ሺህ 470 ሄክታር መሬት በቅመማ ቅመም ዘር ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን እስካሁን 5 ሺህ 615 ሄክታር መሬት ለምቷል። ከልማቱም ከ334 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቀ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም