ኦህዴድ የደረሰበትን የትግል ምዕራፍ የሚያመላከት የስያሜና መለያ ፕሮፖዛሉን ለውይይት አቀረበ

107
አዲስ አበባ ነሐሴ 1/2010 የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦህዴድ) አሁን የደረሰበትን የትግል ምዕራፍ የሚያመላከት ስያሜና መለያ በማስፈለጉ ስያሜውን ወደ ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀይር እንደሆነ ታወቀ። የድርጀቱ ከፍተኛ አመራሮች በፓርቲው ውስጥ የተደረገውን የሱፐርቪዥን ውጤት፣  ስያሜና መለያውን አስመልክቶ የአንድ ቀን ውይይት ኣካሂዷል። የኦህዴድ ጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ከውውይቱ በኃላ እንደተናገሩት ድርጅቱ በዚህ ወቅት ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል። በመሆኑም በዚህ ወቅት ድርጅቱ የደረሰበትን ደረጃ የሚያመለክት መለያና ስያሜ በማስፈልጉ እንዲሁም ኦህዴድ ፓርቲ ቢሆንም ድርጅት ብሎ መጠራቱ ተገቢ አለመሆኑ ስለታመነበት መለወጥ አስፈልጓል ብለዋል። ከዚህ ባለፈ ስያሜው ላይ የሚገኘው ማንም የሚያውቀውን 'ህዝብ' የሚል ቃል አስፈላጊነቱ እምብዛም መሆኑና መለያ ባንዲራውንም በተመለከተ የተለየ ባንዲራ ለምን አስፈለገ የሚል ድምዳሜ ላይ ተደርሷል ነው ያሉት። ከዚህ ባለፈም ለውጡ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በድርጅቱ ስም ሲሰሩ ከነበሩ መጥፎ ተግባራትን ለመርሳት ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ አመልክተዋል። ወይዘሮ አዳነች ውሳኔው በቀጣዩ የፓርቲው ጉባኤ ላይ የሚወሰን ቢሆንም አሁን አባላት እንዲወያዩበት ስሙ ወደ 'ኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ' እንዲቀየር ለውሳኔ ቀርቧል ብለዋል። የጽህፈት ቤት ኃላፊዋ የመለወጥ ሂደቱ ዓለም አቀፍ ሁኔታዎችና ተሞክሮዎችም የተደሳሱበት መሆኑን አብራርተዋል። በሌላ በኩል የድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊዎች በክልሉ የሚስተዋለውን ሕገ ወጥነትን ለማስቆምና ሰላምና ደህንነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንዲሰሩ ውይይት መደረጉን ገልጸዋል። አሁን የተገኙትን መልካም ድሎች መጠበቅና መንከባከብ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊዋ ችግሩ ተባብሶ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይጓዝ አመራሩ በቁርጠኝነት እንዲሰራ ይደረጋል ብለዋል። በተመሳሳይ በቀጣይ አመራሩ የልማት ስራዎች ላይ ማተኮርና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን የማስወገድ ተግባራት እንዲያከናውን ውውይት መደረጉን ገልጸዋል። ችግሮች ሲፈጠሩ፣ ህዝቦች እርስ በርስ ሲጋጩና ሲፈናቀሉ የችግሩን ምንነት የሚተነትን አመራር ያስፈልጋልም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም