አሸባሪው ህወሃት የሽብር ጥቃት በመፈጸም ለትግራይ ህዝብ እርዳታ እንዳይደርስ ማስተጓጎሉ ተገለጸ

60

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ክልል የእርዳታ እህል ጭነው የሚጓጓዙ 189 ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ የሽብር ጥቃት በመፈጸም የእርዳታ መስመር እንዲዘጋ ማድረጉን የብሄራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

አሸባሪው ህወሃት ለትግራይ ህዝብ ርህራሄ እንደሌለው በተግባር እያረጋገጠ መሆኑ ተጠቁሟል።

የብሄራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት፤ ባለፉት ሶስት ቀናት በአፋር በኩል ወደ ትግራይ ክልል በመጓጓዝ ላይ የነበሩ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑ 189 ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ የሽብር ጥቃት በመፈጸም የእርዳታ መስመር ዘግቷል።

በዚህም ምክንያት የሰብዓዊ እርዳታ የጫኑት ከባድ ተሽከርካሪዎች ለመቆም ተገደዋል። 

አሸባሪው ሕወሓት የእርዳታ መስመሩን የዘጋው በአፋር ክልል ዞን አራት ፈንቲረሱ ያሎ ወረዳ በከፈተው የሽብር ጥቃት ነው።

መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ እርዳታ በወቅቱ እንዲደርስ ሁኔታዎችን ማመቻቸቱን ያስታወሱት ኮሚሽነር ምትኩ፤ ለትግራይ ህዝብ ምንም ርህራሄ የሌለው አሸባሪ ሃይል ግን የእርዳታ መስመር በመዝጋት ሰብዓዊ ቀውስ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

መንግስት የዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሚሰጡትን እርዳታ እንዳይስተጓጎልና በወቅቱ እንዲደርስ ሁኔታዎችን ቢያመቻችም አሸባሪው ህወሃት የሽብር ጥቃት ከመፈጸም አለመታቀቡ ተገልጿል።

በዓለም ምግብ ፕሮግራምና ሌሎች ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በኩል ምግብና ምግብ ነክ ያልሆነ የእርዳታ አቅርቦቶች በተገቢው መንገድ ወደ ትግራይ ክልል እንዲያጓጓዙ መንግስት ሁኔታዎችን እያመቻቸ ቢሆንም በቡድኑ የሽብር ጥቃት ምክንያት እየተስተጓጎለ መሆኑ ነው የተገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም