በዞኖቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ህዝቦችን የማቀላቀል ባህላዊ ስርዓት ተካሄደ

71
ዲላ ነሀሴ 1/2010 በምዕራብና ምስራቅ ጉጂ ዞኖች እንዲሁም በጌዴኦ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ተፈጥሮ የነበረውን የፀጥታ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በአጎራባች ወረዳዎች የሚገኙትን ህዝቦች የማቀላቀል ባህላዊ ስርዓት ተካሄደ፡፡ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌና ወናጎ ወረዳዎች በምዕራብ ጉጂ ዞን ደግሞ የአባያ ወረዳ ህዝቦች ለማቀላቀል የተከናወነው ይህ ባህላዊ ስርአት ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም በሁለቱ አባ ገዳዎች ደረጃ የተካሄደው የእርቀ ሰላም ጉበኤ ተከታይ መርሀ-ግብር መሆኑ ተመልክቷል፡፡ "የጌዴኦና የጉጂ ኦሮሞ ህዝብ በፍቅር፣ በአንድነት፣ በይቅርታና በመደመር ጉዞ" በሚል መሪ ቃል በባህል አባቶች አማካይነት የተካሄደው ባህላዊ ሥርአት ይርጋጨፌንና አባያ ወረዳን በሚያዋስነው ሚጪጫ በተባለ ሥፍራ ነው፡፡ ሥርአቱን በጌዴኦ አባቶች በኩል አባ ገዳ ደምቦቢ ማሮ፤ በጉጂ ኦሮሞ አባቶች በኩል ደግሞ የአባ ቃሉ አጋ ሳቆ ተወካይ የሆኑት አባ ሀሎኦ ሞኮና ቃሉ በጋራ ሆነው መርተውታል ፡፡ በባህላዊ ክንዋኔው መሰረት የሁለቱም ባህላዊ መሪዎች በአንድ ላይ ሆነው በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት እንዲሁም የተፈፀሙ ኢሰብዐዊ ድርጊቶችን በማውገዝ ችግሩ ዳግም እንዳይከሰት ለፈጣሪ ፀሎት አድርሰዋል፡፡ እርድ በመፈጸም አብሮ የመብላትና የመጠጣት ሥርዐትም ተከናውኗል ፡፡ የጌዴኦ አባ ገዳ ደምቦቢ ማሮ በዚህ ወቅት እንዳሉት በወንድማማች ህዝቦች መካከል የተፈጠረው ችግር በዘላቂነት ተቀርፎ በሁለቱም ወገን ያሉ ሰዎች ሰላማዊ ኑሮ እስኪጀምሩ ድረስ ከጉጂ አባ ገዳና የባህል አባቶች ጋር ሆነው ጥረታቸውን እንደሚያጠናክሩ ተናግረዋል ፡፡ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላትም ዘላቂ ሠላም ለማረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጠይቀዋል ። ወጣቶች የነገ አገር ተረካቢዎች በመሆናቸው ከእኩይ ተግባራት ተቆጥበው በትምህርትና በልማት ሥራዎች በንቃት ከመሳተፍ ባለፈ ለባህላቸውም ተገዢ መሆን እንደለባቸው አሳስበዋል ፡፡ ሁለቱም ህዝቦች ለሠላም ቅድሚያ መስጠት እንዳለባቸው ያመለከቱተ አባ ገዳ ደምቦቢ ማሮ በመካከላቸው ፀብ የሚዘሩ አካላትን ለሕግ አሳልፈው እንዲሰጡ  አስገንዝበዋል፡፡ የኦሮሞ አባ ቃሉ ተወካይ አባ ሀሎኦ ሞኮና ቃሉ በበኩላቸው የጌዴኦና ጉጂ ህዝቦች ከጥንት ጀምሮ ልዩነት ሳይፈጥሩ ተጋብተውና ተዋልደው የኖሩ መሆናቸውን ገልጸዋል። ጥቂት ግለሰቦች የመከፋፈል ሀሳብ በማሰራጨታቸው ምክንያት በመካከላቸው ችግር መፈጠሩን ገልፀው በአሁኑ ወቅት የሰፈነው አንጻራዊ ሠላም ቀጣይነት እንዲኖረው ህዝቡ ቂም ትቶ የቀደመውን አንድነቱን ጠብቆ መኖር እንዳለበት አመልክተዋል ፡፡ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በበኩላቸው ዳግም የተፈጠረውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሁለቱ አባ ገዳዎች በጋራ ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። የችግሩን መንስኤ ለማወቅና አስተማማኝ መፍትሄ ለማበጀት መንቀሳቀሳቸውንና በባህል አባቶች ደረጃም የዕርቀ ሠላም ጉባኤ መካሄዱን አስታውሰዋል፡፡ በአጎራባች ወረዳ ህዝቦች መካከል በየደረጃው እየተካሄዱ ያሉ የእርቀ ሰላም መድረኮችም የእዚሁ አካል መሆናቸውን ነው የጠቆሙት ፡፡ እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለጻ አሁን ባለው ሁኔታ ሠላም በሰፈነባቸው አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው በመመለስ ላይ ናቸው ፡፡ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን ለማድረግ በባህል አባቶች በኩል ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን ከፌዴራል እንዲሁም ከሁለቱም ክልሎችና ዞኖች የተወጣጡ አካላት በጋራ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ በአካባቢው ፀጥታን ለማስከበርና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፖሊስ ተቀናጅተው እየሠሩ መሆናቸውንም አመልክተዋል ፡፡ የምዕራብ ጉጂ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ እንዳሉት በዞኑ እስከ ቀበሌ ድረስ ያሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የማወያየት ሥራ በመሰራቱ አሁን ላለው አንፃራዊ ሰላም አስተዋፅኦ አበርክቷል ፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቄያቸው ሲመለሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ቤታቸውን በመስራትና በመርዳት እያገዟቸው መሆኑን ጠቁመው በዘላቂነት ለማቋቋም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር እንደሚሰራ አስረድትዋል፡፡ ከባህላዊ ሥርዓቱ ታዳሚዎች መካከል በምዕራብ ጊጂ ዞን የአባያ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ጌጤ ሙርከታ ሠላም ሲደፈርስ ዋነኛ ተጎጂዎች ሴቶችና ሕፃናት መሆናቸውን ተናግራለች ፡፡ "ከዚህ በኋላ ከኋላችን ሆነው እኛን ለግጭት የሚያጋፍጡን ፀረ ሰላም አካላት መጠቀሚያ አንሆንም" ብላለች፡፡ በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ነዋሪ ወጣት ጴጥሮስ በራሶ በበኩሉ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ሠላም በመውረዱ መደሰቱን ገልፆ ከሁለቱም ወገን የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ሲመለሱ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጿል፡፡ በቀጣይም በሌሎች አጎራባች ወረዳዎች የሚገኙ ዜጎችን ለማቀላቀል ተመሳሳይ የእርቀ ሠላም መደረኮች እንደሚካሄዱ ታውቋል ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም