የእርቀ ሠላም መድረኮች የሚመሩ በህብረተሰቡ ተቀባይነት ሊኖራቸው እንደሚገባ ተጠቆመ

59

አሶሳ ፤ ሐምሌ 13/2013 ( ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉመዝ ክልል መተከል ዞን ግጭትን ለመከላከል የሚካሄዱ የእርቀ ሠላም መድረኮችን የሚመሩ አካላት በአካባቢው ህብረተሰቡ ተቀባይነት ያላቸው ሊሆኑ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡

በግጭት መከላከል እና እርቀ ሠላም ላይ ያተኮረ ውይይት በአሶሳ ከተማ ተካሂዷል፡፡

 ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አዲሱ አስኔ እንዳሉት፤  በክልሉ ግጭትን ለመፍታት በርካታ የእርቀ ሠላም መድረኮች ተካሂደዋል፡፡

ውጤትም ተገኝቶባቸዋል ብለዋል፡፡

 ይሁንና በቅርቡ እርቀ ሠላም በተካሄደባቸው አንዳንድ የመተከል አካባቢዎች ግጭቶች እንደገና የሚከሰቱበት አጋጣሚዎች መኖራቸውን ተሳታፊው ጠቁመዋል፡፡

እንደ አቶ አዲሱ ገለጻ፤ እርቀ ሠላም በተካሄደባቸው አካባቢውች ግጭት እንደገና የሚከሰተው የእርቀ ሠላም መድረኮችን የሚመሩ አካላት በህብረተሰቡ በሚገባ ተቀባይነት የሌላቸው ግለሰቦች ጭምር በመሳተፋቸው ነው፡፡

እርቀ ሠላም ከመካሄዱ በፊት የውይይት መድረኮችን የሚመሩ ግለሰቦች በጥናት ተለይተው  በህብረተሰቡ ተቀባይነት ያላቸው ስለመሆኑ ማረጋገጥ  እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

 ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ ወይዘሮ እመቤት ኦላና  በበኩላቸው በእርቀ ሠላም መድረኮች በህብረተሰቡ የሚነሱ ሃሳቦች በሚገባ ወደ ተግባር በመቀየር   ግጭት እንዳይከሰት በማድረግ ረገድ ክፍተት እንዳሉ ተናግረዋል፡፡

በተለይ መንግስታዊ አካላት ከውይይት መድረክ ባለፈ ሲቪክ ማህበራትን እና ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ በተግባር የተደገፈ ቅንጅታዊ አሰራር መከተል እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል፡፡

የአሶሳ ከተማ  ሃይማኖት ተቋማት ህብረት ሰብሳቢ ሃጂ ሃምደኒል መሃመድ ፤  ዘላቂ ሠላምን ለማስፈን ልጆቻችንን  የማስተማር  ጠንካራ  ስራ ይጠብቀናል ብለዋል፡፡

የውይይት መድረኩን የመሩት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ የግጭት መከላከል እና አፈታት ዳይሬክተር አቶ ኮማንደር ወርቁ ፤በክልሉ  አንዳንድ አካባቢዎች ለሚከሰቱ ግጭቶች የማህበረሰቡ የሠላም እሴቶች መሸራረፍ ዋነኛ ምክንያቶች እንደሆኑ  ገልጸዋል፡፡

የግለሰቦች አግባብ ያልሆነ ጥቅም ፍላጎት፣ ፍትሃዊ ያልሆነ የሃብት ክፍፍል እንዲሁም ጁንታው የህዳሴውን ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ የያዘው ሴራም ሌላው ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ግጭቶችን ለመፍታት በሚካሄዱ መድረኮች የሚሳተፉ አንዳንድ የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግዎች እና ታዋቂ ግለሰቦች የፖለቲካ ወገንተኝነት እና የግል ጥቅምን ማስቀደም እንደሚታይባቸው ጠቁመዋል፡፡ 

የክልሉ መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስፈን ከመተከል ኮማንድ ፖስት ጋር በጋራ ሲሠራ መቆየቱን አስታውሰው ፤ውጤት እንደተገኘበትም ዳይሬክተር አብራርተዋል፡፡

ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ሳይንሳዊ የግጭት አፈታትን ከአካባቢው እውነታ ጋር አጣጥሞ በመሄድ ረገድ ግን ቀሪ ስራዎች እንዳሉ ገልጸዋል።

መንግስታዊ አካላት በተለይ ወጣቱ ወደ ስራ ፈጠራ የሚገባባቸውን  መስኮች በማስፋት ግጭት እንዲቀነስ የድርሻቸውን እንዲወጡ አቶ ኮማንደር መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም