አስተዳደሩ ለምርጫው ሰላማዊነት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋናና እውቅና ሰጠ

87

ድሬዳዋ፣ ሐምሌ 12/2013 (ኢዜአ) የድሬዳዋ አስተዳደር ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋናና እውቅና ሰጠ፡፡

በድሬዳዋ አስተዳደር በተከናወነው ምርጫ 10 የፖለቲካ  ፓርቲዎችና  ሁለት የግል  ተወዳዳሪዎች የተሣተፉ ሲሆን ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ  ሆኖ  መጠናቀቁ  ተመልክቷል፡፡

አስተዳደሩ ምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፍትህና የፀጥታ አካላት፣ የሲቪክ ማህበራትና የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዕውቅናና ምስጋና እንዲሁም  የምስክር ወረቀት  የሰጠበት  ስነ ስርአት  አከናውኗል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡህ  በስነ ስርአቱ  ላይ ዕውቅናና ምስጋና የተቸራቸው ባለድርሻ አካላት ለምርጫው ስኬታማነት ያደረጉትን አስተዋጻ  በአስተዳደሩ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም በሚከናወኑ ተግባራት ውስጥ  እንዲደገሙ  ጠይቀዋል፡፡

በተለይ ድሬዳዋን የምስራቁ የሀገሪቱ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግና ሥራ እጥነትን ትርጉም ባለው መንገድ ለመቀነስ በሚከናወኑ ተግባራት ወሳኝ ድርሻ እንደሚኖራቸው አመላክተዋል።

''ለድሬዳዋ ዘላቂ ሰላምና ዕድገት ተቀናጅተንና ተባብረን መስራት ይኖርብናል''  ብለዋል፡፡

ምስጋናና ዕውቅና የተሰጣቸው የተፎካካሪ ፓርቲዎችና ሌሎች አካላት ከሁሉም በላይ ሀገርን በማስቀደምና ልዩነቶችን በማክበር  ኢትዮጵያን  ለማሻገር  የሚጠበቅባቸውን  ሁሉ  እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል፡፡

በአስተዳደሩ በምርጫው የተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) የድሬዳዋ ተወካይ  አቶ ዮናስ  በትሩ  የእውቅና  ስነ ስርአቱ  ''መቀራረብና በጋራ ተባብሮ መስራትን የሚጋብዝ ነው" ብለዋል፡፡

የድሬዳዋ የቀድሞ ታላቅ የአንድነት መንፈስ እንዲፈጠር ፣ በፍቅርና በእኩልነት ተከባብረው የሚኖሩባት ከተማ እንድትሆን ተግተው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

ድሬዳዋን ዳግም የኢንዱስትሪና የአገልግሎት  ማዕከል ለማድረግ በትብብር  መስራት  እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል፡፡

ለድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት የተካሄደውን ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ ሙሉ በሙሉ ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሁለት መቀመጫዎች በተደረገው ምርጫ ደግሞ አንዱን ብልጽግና ፓርቲ ሲያሸንፍ፣ የሌላኛው መቀመጫ ጉዳይ በሂደት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በኢትዮጵያ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተካሄደው ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓም መሆኑ ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም