በአሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገሪቱ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ነን...የጌዴኦ ነዋሪዎች

108

ዲላ፣ ሐምሌ 12/2013 (ኢዜአ) በጌዴኦ ዞን የሚገኙ ነዋሪዎች በአሸባሪው የህወሓት ቡድን በሀገሪቱ ላይ የተቃጣውን ጥቃት ለመመከት አስፈላጊውን መስዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን አስታወቁ።

የዞኑ ነዋሪዎች የአሸባሪውን የህወሓት ቡድን ትንኮሳ ያወገዙበትን ሰልፍ ዛሬ በዲላ ከተማ  አካሂደዋል።

በዲላ ከተማ የሚገኙ የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን፣ የመንግስት ሰራተኞች፣ የወረዳና የከተማ መዋቅር አስተዳዳሪዎች፣ የፖሊስ ሰራዊት አባላት እና የዲላ ከተማና  አካባቢው ነዋሪዎች በሰልፉ ተሳትፈዋል።

"ሰልፈኞቹ ለሀገር መከላከያ ሠራዊታችን ደጀን እንሆናለን፣ የአሸባሪውን የህወሃት ትንኮሳ እናከሽፋለን፣  ክብርና ሞገስ ለመላው የፀጥታ ሀይላችን" የሚሉና ሌሎች መፈክሮችን በማሰማት የቡድኑን ትንኮሳ አውግዘዋል።  

ከሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል የቆፌ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ8ኛ ክፍል ተማሪ መሳይ ወርቁ ህወሓት በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጆ ታዳጊዎችን ማስታጠቁን ለማውገዝ ሰልፍ መውጣቱን ተናግሯል።

ታዳጊዎች ከጦር ግንባር ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ፍላጎቱ መሆኑን  ጠቅሶ፤ ፍላጎቱ እውን እንዲሆን ባገኘው አጋጣሚ ድምጹን ለማሰማት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል።

"ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን የተቃጣብንን ጥቃት በመመከት በድል ለማጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ" ያሉት ደግሞ  የዲላ ከተማ ፓሊስ አባል ሳጅን አሸናፊ አለማየሁ ናቸው።

ሀገራዊ ጥሪን ተቀብለው  በግንባር ለመሰለፍ  ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪ አቶ ምትኩ በላይ በበኩላቸው ኢትዮጵያ አቅሙ በተዳከመ አሸባሪ ቡድን ልትፈርስ እንደማትችል ገልጸዋል።

አሸባሪውን የህወሓት ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ የሀገር ነቀርሳነቱን ለማስቆም አስፈላጊውን መስዋትነት ለመክፍል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የጌዴኦ ዞን ዋና አስተደደሪ አቶ ሽፈራው ቦጋለ እንዳሉት ህወሓት በሰለጠኑና በታጠቁ ወታደሮች ያጣውን ድል ህጻናትን በመማገድ አገኛለሁ ብሎ ማሰቡ ድርብ ስህተት መሆኑን አመልክተዋል።

የዞኑ ህዝብና መንግስት ከዚህ ቀደም የህግ ማስከበር ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ ያሳየውን ድጋፍ አሁንም በመድገም ለመከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን እንደሚያሳይ  ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም