ኦነግ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሰላማዊ መንገድ አገር ውስጥ ገብቶ መንቀሳቀስ የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራረመ

79
አዲስ አበባ ሀምሌ 1/2010 የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሰላማዊ መንገድ ወደ አገር ውስጥ ገብቶ መንቀሳቀስ የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል። መንግስት ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው በሰላም እንዲታገሉ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ፍጻሜ ለማድረስ ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። በዚህም በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ መንገድ ለመታገልና ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ወደ ሀገር ቤት ተመልሰዋል፤ እየተመለሱም ነው። የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ትናንት በሰጡት መግለጫም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ የሚመራ የልኡካን ቡድን በኤርትራ በዳውድ ኢብሳ የሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር ለመወያየት ወደ አስመራ እንዳቀኑ መግለጻቸው ይታወሳል። ልዑካን ቡድኑም ከነጻነት ግንባሩ ጋር ለሁለት ቀናት ባደረጉት ውይይት ኦነግ በሰላማዊ መንገድ ከኢትዮጵያ መንግስት አንዲሁም ከኦሮሚያ መንግስት ጋር በኦሮሚያና ኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ እየተወያያ በሰላማዊ መንገድ አንደሚሰራ መወሰኑን ገልጸዋል። በውሳኔው መሰረትም በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከስምምነት መድረሳቸውን ተናግረዋል። በዚህም ኦነግ ለበርካታ ዓመታት ሲያካሄድ የቆየውን የትጥቅ ትግል በማቆም በሀገሪቱ በተፈጠረው መልካም አጋጣሚ ትግሉን በሰላማዊ መንገድ ለመቀጠል ከስምምነት ተደርሷል። ስምምነት የተደረሰባቸውን ጉዳዮች ስራ ተግባራዊ ለማድረግና ዝርዝር ጉዳዮችን በተመለከተም ከሁለቱም የተውጣጡ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደፊት አስፈላጊ የሆነ ውይይት እንደሚቀጥል መስማማታቸውንም ነው የጠቆሙት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም