የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት ለማጠናከር መዘጋጀታቸውን የዳውሮ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ

75
ሶዶ ሀምሌ 1/2010 መንግስት የጀመረውን አገራዊ የለውጥ ጉዞ በመደገፍ የአካባቢያቸውን ሰላምና ልማት ለማጠናከር መዘጋጀታቸውን የዳውሮ ዞን ነዋሪዎች ገለጹ። የዞኑ አስተዳደር በበኩሉ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚያሳትፍ አደረጃጀትና አሰራር በመዘርጋት የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን የመደመርና የይቅርታ መርህ እንደሚያስቀጥል ገልጿል፡፡ የዞኑ ወጣቶች ለረዥም ጊዜ የተጓተተውን የተርጫ-ወልደሃና ዱርጊ-ዱራሜ መንገድን ለመስራት ያሳዩትን ተነሳሽነት ነዋሪዎቹ በአካል ተገኝተው በማበረታታት ድጋፋቸውን አሳይተዋል፡፡ የተርጫ ከተማ ነዋሪ ወይዘሪት ሰገነት ዱሬሳ በበኩላቸው መንግስት በመደመር መርህ የጀመራቸው የለውጥ ሥራዎችን በተግባር ለመደገፍ ከርቀት መጥተው በመንገድ ልማት ሥራው መሳተፋቸውን ተናግረዋል፡፡ የአካባቢያቸው ልማትና ሰላም ቀጣይነት እንዲኖረው ባላቸው አቅም ሁሉ ጠንክረው ለመሳተፍና በተግባር ለመደፈግ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገሪቱ ላመጡት ለውጥ የአካባቢው ማህበረሰብ በልማት በመሳተፍ በተግባር መደመሩን እንዲያረጋግጥ ሲያነሳሱ መቆየታቸውንና እርሳቸውም በስራው መሳተፋቸውን የተናገሩት ደግሞ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ መምህር የሆኑት ዱባለ ገበየሁ ናቸው፡፡ ከአጎራባች ዞኖች የሚያገናኝ መንገድ በመዘጋቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ደርሶ እንደነበረም አስታውሰዋል። የአካባቢው ነዋሪና የመድረክ ፖለቲካ ድርጅት አባል አቶ ዳሮታ ዶጃሞ በበኩላቸው በተለያዩ የፖለቲካ አደረጃጀቶች መንግስትን  ሲቃወሙ ቢቆዩም በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የተፈጠረውን የለውጥ እንቅስቃሴ መደገፋቸውን ገልጸዋል፡፡ "ወጣቱ  የአከባቢውን ልማት ለማረጋገጥ  በመንገድ ልማት ስራ በተነሳሽነት በመሳተፍ መንግስትን መደገፍ መጀመሩ የመደመር ማሳያ ነው" ያሉት አቶ ዳሮታ ጅማሬው አገራዊ ልማቱን ለማስቀጠል ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡ ለውጥን መደገፍና መደመር ማለት በየዘርፉ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለመድፈን ተግባራዊ ሥራ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ የአካባቢያቸውን ሰላም ለማጠናክር የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበበ አታሮ በአካባቢው ተፈጥሮ የነበረው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለልማቱ ማነቆ ከመሆንም በላይ አለመግባባቶች እንዲስፋፉ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ የወጣቶችን የልማት ተነሳሽነት ያደነቁት አቶ አበበ ዞኑ ህዝቡ የሚያነሳቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች በማስወገድ አሳታፊ በሆነ መልኩ የአካባቢውን ልማት፣ ሰላምና የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል፡፡ በቀጣይም በዳውሮ ወጣቶች የተጀመረውን የታርጫ-ወልዴሃኒ ዱርጊ-ዱራሜ መንገድ ሥራ የዞኑ አስተዳደር ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዕለቱ የተለያዩ አቋም በማራመዳቸው ታስረው የተፈቱ አካላትና የዞኑ አመራር በአካባቢው ህብረተሰብ ዘንድ የተፈጠረውን ቅሬታ ለመፍታት በጋራ እንደሚሰሩ በህዝብ ፊት እጅ ለእጅ ተያይዘው አረጋግጠዋል፡፡  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም