የኮቪድ-19 ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ የጤና ባለሙያዎችና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች እውቅና ተሰጠ

55

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 11 ቀን 2013 (ኢዜአ) የኮቪድ-19 ወረሽኝን በመከላከል ረገድ ኃላፊነታቸውን ለተወጡ የጤና ባለሙያዎችና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች እውቅና ተሰጠ።

የጤና ባለሙያዎችና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች ሀገር አቀፍ የምስጋናና የዕውቅና ሳምንት የማስጀመሪያ መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ ወዳጅነት አደባባይ ተካሄዷል።

በመረሃ-ግብሩ ላይ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና  ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የምስጋናና የዕውቅና ሳምንቱ ከሐምሌ 11 እስከ ሐምሌ 17 ቀን 2013 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን፤ የጤና ባለሙያዎች እና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች  የህይወት መስዋትነት በመክፈል ጭምር  የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመቀነስ ያደረጉትን ጥረት ለመዘከር ያለመ ነው።

የምስጋናና እውቅና መርሃ ግብሩ በሁሉም በክልሎችና ከተማ መስተዳድሮች እንዲሁም በየደረጃው ባሉ ተቋማት እንደሚከበርም ተገልጿል።

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ባስተላለፉት መልዕክት የጤና ባለሙያዎቹ  ለውድ ህይወታቸው ሳይሰስቱና የግል ፍላጎታቸውን ወደ ጎን በመተው የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል ዋጋ መክፈላቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም ጤና ባለሙያዎችና የጤና ክብካቤ ሰራተኞች ለከፈሉት መስዋትነት እውቅና መስጠት ተገቢ ነው ብለዋል።

ባለሙያዎቹ ህዝባቸውን ከከፋ ጉዳት የታደጉ የጤና ጀግኖች ናቸው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ሀገርና ለህዝብን ለመታደግ ለከፈሉትና እየከፈሉ ላሉት መስዋዕትነት ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ይበልጥ ለማሻሻል ተቀናጅተን መስራት አለብን ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን ፈተናን ማለፍ ብቻ ሳይሆን አልፈው ድል መዘከርን ያውቁበታል ነው ያሉት።

በኮቪደ-19 ወረሽኝን ለመከላከል እንዲሁም  የሀገርን ህልውና ለመጠበቅ በግንባር እየተዋደቁ ያሉ ጀግኖችን መዘከር እንደሚገባ ገልጸው፤ የቫይረሱን ስርጭት በመከላከል ረገድ የበኩላቸውን ሚና ለተወጡ የጤና ባለሙያዎች ምስጋና አቅርበዋል።

መንግስት ጤናማ ማህበረሰብ ለመፍጠር እያደረገ ያለው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።

በመርሃ ግብሩ የኮቪድ-19 ቫይረስ ወረርሽኝ ምላሽ አሰጣጥ ላይ ለተሳተፉ የጤናው ዘርፍና ሌሎች ተቋማት እውቅና ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም