በ175 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙ የተለያዩ ዘመናዊ መሳሪያዎች ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተበረከቱ

67
አዲስ አበባ ሀምሌ 1/2010 የአዲስ አበባ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ለመንገድ ትራፊክ ቁጥጥር አጋዥ የሆኑ ተሽከርካሪዎችንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሰጥቷል። የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም ባንክ ባገኘው በረጅም ጊዜ የሚመለሰ ብድር አማካይነት በ175 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገዙ  የተለያዩ ተሽከርካሪዎች፣ ሞተር ሳይክሎችና ሌሎች ዘመናዊ መሳሪያዎች ናቸው ለኮሚሽኑ የተበረከቱት። በዚህም በዛሬው እለት ርክክብ የተደረገባቸው 275 ሞተር ሳይክሎች ፣ 2 አምቡላንሶች፣ 4 ፒክ አፕ መኪናዎች፣ 26 ሚኒባሶች፣ 100 ዘመናዊ መረጃ የተጫነባቸው ስማርት ስልኮች፣ ራዳሮችና ሌሎች ዘመናዊ ቁሳቁሶች ናቸው። ስልኮቹ በከተማዋ የሚከሰተውን የመንገድ ትራፊክ አደጋ መከታተልና መቆጣጠር ብሎም ለመቅጣት የሚያስችል አፕልኬሽን የተጫነባቸው ዘመናዊ ሞባይሎች ናቸው። የመንገድ ትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የከተማዋን የመሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ስርዓትን ለማሻሻል ብሎም የዘርፉን ተቋማት የማስፈጸም አቅም ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ያሉት የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጅነር ሰለሞን ክዳኔ ናቸው። የትራፊክ ፖሊስን በዘመናዊ አሰራሮችና መሳሪያዎች በመደገፍ አሁን በከተማው ውስጥ የሚታዩ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቆችንና የትራፊክ አደጋዎችን ለመቀነስ እንዲሁም የትራፊክ ደንብና መመሪዎችን በላቀ ሁኔታ ለማስፈጸም ችግሩን በበቂ ሁኔታ ለመፍታት ያስችላሉ ብለዋል። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በበኩላቸው የተሰጠው ዘመናዊ መሳሪያ የፖሊስን ስራ በዘመናዊ መልኩ ለማከናወን ያስችላል ብለዋል። ከዚህ በፊት በመሳሪያ ቁጥጥር የሚከሰቱ ችግሮችን በመፍታት የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠትም እንደሚያስችላቸው ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም