በሱማሌ ክልል የተፈፀመውን ጥቃት የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አወገዘ

61
አዲስ አበባ ነሀሴ1/2010 በኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ዘርና ኃይማኖትን መሰረት በማድረግ የተፈፀመውን ጥቃት የአዲስ አበባ ኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አወገዘ። የጉባኤው ዋና ፀሐፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በሚገኙ ወገኖች ላይ የተፈፀመው የህይወት መጥፋት፣ የአብያተ ክርስትያናትና የንብረት ውድመት እጅግ አሳዛኝና ልብ የሚሰብር ተግባር ነው። ይህ ተግባር ህገ-ወጥ እና ኢሰብዓዊ በመሆኑ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤው አጥብቆ እንደሚያወግዘው መጋቤ ታምራት አስታውቀዋል። በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል የአንድነትንና የይቅርታ መንፈስን ለማስፈን በመላው ሀገሪቱ እንቅስቃሴ በተጀመረበት በአሁኑ ወቅት ይህ ተግባር መፈጸሙ እጅግ አሳዛኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል። መንግስት የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነቱን በአፋጣኝ እንዲወጣም ጉባኤው  አሳስቧል። ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለማቋቋም በቅንጅት መስራት እንደሚገባም ዋና ፀሐፊው አስገንዝበዋል። በክልሉ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ቀድሞ ወደ ነበረበት እንዲመለስ ለማድረግም የሐይማኖት ተቋማትን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና ኡጋዞችን ጨምሮ መላው ህብረተሰብ እንዲረባረብ ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል። የአገሪቱን ሰላም ለማወክ ታስቦ የሚፈጸመው ይህን የመሰለ ድርጊት ለመከላከል ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዘብ በመቆም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባም ዋና ፀሐፊው አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም