የአፋር ክልላዊ መንግስት 117 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ መፍታቱን አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
የአፋር ክልላዊ መንግስት 117 የህግ ታራሚዎች በይቅርታ መፍታቱን አስታወቀ
131
ሰመራ ነሀሴ 1//2010 የአፋር ክልላዊ መንግስት በተያዘው ወር የሚከበረው የኢድ አል አድሃ(አረፋ) በዓል ምክንያት በማድረግ ለ117 የህግ ታራሚዎች ትናንት በይቅርታ መፍታቱን የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቢሮው ኃላፊ አቶ አሊ መሐመድ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ወንጀሎች ተከሰው በማረሚያ ቤት ያሳለፉ የህግ ታራሚዎች ባሳዩት የስነ-ምግባር መሻሻል በይቅርታ በመፍታት ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በሀገሪቱ በተጀመረው የአንድነትና ይቅርታ መንፈስ ተከትሎ የክልሉን መንግስት የይቅርታ አሰጣጥ ህጉን መሰረት በማድረግ ለ117 ታራሚዎች በይቅርታ መፈታታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የተፈቱት የህግ ታሪሚዎች በይቅርታ መፈታታቸው የህብረተሰቡን ሰላምና ልማት ለማረጋገጥ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ውስጥ በባለቤትንት መንፈስ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል፡፡ ይህ እድል የይቅርታ ህጉ በሚያዘው መሰረት ከሙስናና ከአስገድዶ መድፍር ወንጀል ጋር ተያይዞ ተከሰው የፍርድ ውሳኔ የተሰጣቸው ታራሚዎችን አያካትትም፡፡ በይቅርታ ከተፈቱት የህግ ታራሚዎች መካከል ከአውሲረሱ ማረሚያ ቤት የድሉ ተጠቃሚ የሆነው አዱልቃድር አሊ በማረሚያ ቤት ቆይታው ህጋዊ መብትና ግዴታውን በተገቢው በመገንዘብ ከጥፋቱ መማሩን ተናግሯል፡፡ የክልሉ መንግትት ባደረገለት የይቅርታ እድል ተጠቅሞ ቀሪ ህይወቱን በተገቢው ከመምራት ባለፈ በአካባቢው ልማትና የሰላም እሴት ግንባታ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ እንደሚያደረግም አስረድቷል፡፡ ከዚሁ ማረሚያ ቤት በይቅርታ የተፈታው ኑሩ ሰይድ በበኩሉ በቆይታው ባገኘው የንቃተ-ህግና የሙያ ስለጠና በቀጣይ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ስሙን ለማደስ እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡ በአፋር ክልል ባለፉት አምስት ዓመታት ከ400 በላይ የህግ ታራሚዎች በይቅርታ መፈታታቸውን ከክልሉ ፍትህ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡