በአዲስ አበባ የሃይል መቆራረጥ ችግር ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ተጠየቀ

112

አዲስ አበባ ሐምሌ 09 ቀን 2013 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ ሃይል መቆራረጥ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ተጠየቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የሃይል መቆራረጥ ዋነኛ መንስኤው የማስተላለፊያ መስመሮች እርጅና በመሆኑ ለማሻሻል እየተሰራ መሆኑን አስታውቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ቢሮ በመዲናዋ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ከህብረተሰቡ የሚነሱ ቅሬታዎችንና ችግሮችን ለመፍታት ከተቋቋመው ፎረም ጋር መክሯል።

በምክክሩ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በተገናኘ የሚሰሩ የሚመለከታቸው አካላት የተገኙ ሲሆን በከተማዋ ከሃይል አቅርቦት ጋር የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን አንስተዋል።

የግብአት አቅርቦት ችግር፣ ተናቦ አለመስራት፣ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ቅሬታዎች ፈጣን ምላሽ አለመስጠትና ሌሎች የመልካም አስተዳደር ችግሮች ማህበረሰቡን ክፉኛ እያማረሩ መሆኑን በመደረጉ ተነስቷል።

የኤሌክትሪክ ሃይል ማስላላፊያ ገመዶች መውደቅና አደጋ ማድረስ፣ የሃይል ማስተላላፊያ ተሸካሚ ምሰሶዎች ማርጀትና መውደቅ፣ የሎጂስቲክ እጥረትና ሌሎችንም በማንሳት ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም በተደጋጋሚ የፊውዝ መቃጠል፣ የክፍያ ጣቢያዎች እጥረት፣ የክፍያ ጭማሪ፣ የአገልግሎት አለመዘመንና ሌሎች አገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ ሊያደርጉት እንዳልቻሉም ከተሳታፊዎች ተነስቷል።

የአዲሰ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ነጋሽ ባጫ፤ የተነሱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለህብረተሰቡ መረጃ ሳይሰጥ የኤሌክትሪክ አግልግሎት እንዳይቋረጥ ማድረግ፣ የአሰራር ተጠያቂነት ስርአትን ማጠናከርና አገልግሎትን ማዘመን ቀጣይ ትኩረት ይደረግባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው የከተማዋ የሃይል መቆራረጥ ችግር በሃይል ማስተላለፊያ እርጅና የሚከሰት በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከፊውዝ መቃጠል ጋር በተገናኘ የሚስተዋሉ ችግሮች በጥናት የሚፈቱ መሆኑን ጠቅሰው ከታሪፍ ጭማሪ ጋር የተነሳውን ችግርም የህብረተሰቡን አቅምና የአጠቃቀም ያገናዘበ መሆኑን አስረድተዋለ።

ፎርሙ ከተመሰረተበት የካቲት ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር በተገናኘ የተፈቱ ችግሮች ላይ በመምከር በቀጣይ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም