በአዲስ አበባ የተገነቡት የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጥ በተጨማሪ የስርቆት ስጋትን አስቀርተዋል

58
አዲስ አበባ ሀምሌ 1/2010 በአዲስ አበባ በተመረጡ ዋና ዋና ቦታዎችና የንግድ ማእከላት የተገነቡት የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች የትራፊክ ፍሰቱን ከማሳለጣቸው በተጨማሪ የስርቆት ስጋትን አስቀርተዋል። በሌላ በኩል ግንባታቸው በተያዘላቸው ጊዜ ያልጠተጠናቁ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች እንዳሉም ተገልጿል። በከተማዋ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ አንድ አመት ያስቆጠረው የመገናኛ ተሽከርካሪ ማቆሚያ በቀን በአማካኝ 500 ተሽከርካሪዎችን እያስተናገደ ነው። በ40 ሚሊዮን ብር የተገነባው ይህ አገልግሎት መስጫ ስፍራ ስራ ከመጀመሩ በፊት በአካባቢው መንገድ ዘግተው የሚቆሙ ተሽከርካሪዎች በትራፊክ ፍሰቱ ላይ ጫና ይፈጠር ነበር። የተሽከርካሪ ማቆሚያው ተጠቃሚዎችም አገልግሎቱን መጠቀም ከመጀመራቸው በፊት የተለያዩ ንብረቶች ይሰረቁባቸው እንደነበርና አሁን በአገልግሎቱ መጀመር ምክንያት ከዚህ ስጋት መላቀቃቸውን ገልጸዋል። መሰል አገልግሎት መስጫ ማቆሚያ በሌሎች ዋና ዋና ቦታዎችም ቢስፋፋ የንብረታቸውን ደህንነት መጠበቅ እንደሚችሉ ጨምረው ገልጸዋል። አስተያየታቸውን ከሰጡ አሽከርካሪዎች መካከል በረከት ግርማ እንዳለው"ልዩነቱ አቁመሽው ስትመጪ እርግጠኛ አይደለሽም ሰው ሊሰርቀው ይችላል አላርምም አድርገሽ  ምናምን ነው የምትመጪው ምክንያቱም ሰውም ሊገጭብሽ ይችላል በሌለሽበት”  "ፓርክ አድርጌ የፈለኩት ቦታ እሄዳለሁ ምክንያቱም ምንም አልሰጋም እና ሌላ ቦታም ቢስፋፋ አሪፍ ነው "የሚለው ደግሞ አሽከርካሪ ዳንኤል አሊ ነው ፡፡  ቦታዎቹን የሚያስተዳድረው የአዲስ አበባ መንገድ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ታመነ በሌ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታው የተፈለገውን ለውጥ እያመጣ መሆኑን በህዝብ አስተያየትና በጥናት ማረጋገጡን ተናግረዋል። የተሽከርካሪ ማቆሚያው በአንድ አመት ውስጥ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ገቢ ያስገኘ ሲሆን በቀን የሚገኘው ከ6 ሺህ በላይ ብር የስራ እድል የተፈጠረላቸው 26 ሰዎች 50 በመቶውን ይወስዳሉ። በአንድ ጊዜ እስከ 43 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችለው የወሎ ሰፈር የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት እየሰጠ ነው። ይሁንና በአንድ ጊዜ 180 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችለው አንዋር መስኪድ አካባቢ የሚገኘው አገልግሎት መስጫ ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ለማስገባት ዝግጅት እየተደረገ ነው። በሌላ በኩል ቅድሚያ ተሰጥቷቸው ይገነባሉ ከተባሉት ውስጥ አንዱ በ43 ሚሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው ቸርችል የተሽከርካሪ ማቆሚያ በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ስራ ለማስጀመር ቢታቀድም እስካሁን አልተጠናቀቀም። በተመሳሳይ በሌሎች ቦታዎች እየተገነቡ የሚገኙ የተሽከርካሪ ማቆሚያዎች በውጭ ምንዛሬ እጥረትና በወሰን ማስከበር ችግሮች  ግንባታቸው መዘግየቱን ግንባታውን የሚያከናውነው የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል። በጽህፈት ቤቱ የመሰረተ ልማት ክፍል ኃላፊ አቶ ትንሳኤ ወልደገብርኤል እንዳሉት በተለያዩ ችግሮች ምክንያት በከተማይቱ የሚገነቡ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች በእቅዱ መሰረት ሙሉ ለሙሉ እየተገነቡ አይደለም። የመሬት ላይና መካኒካል ወይንም ስማርት የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎችን የያዘውና በአንድ ጊዜ 125 ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችለው የቸርችል ተሽከርካሪ ማቆሚያ ከሁለት ወር በኋላ ወደ ስራ እንደሚገባ ገልጸዋል። በአዲስ አበባ መሪ እቅድ መሰረት 60 የተሽከርካሪ ማቆሚያ ቦታዎች የተለዩ ሲሆን እነዚህም በመንግስት አቅም ብቻ የሚገነቡ ሳይሆኑ የግል ባለሃብቱንም በማሳተፍ የሚከናወኑ ናቸው። የግል ባለሃብቱ የሚሳተፍበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም የአዋጭነት ጥናቶች የተደረገ ሲሆን ደንብና መመሪያዎች ተዘጋጅተው ለሚመለከተው አካል ምላሽ እንዲያገኝ ተልኳል። በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ባለኃብቶች መመሪያው ምላሽ ሲያገኝ በቀጣዩ አመት ወደ ስራ እንደሚገቡም ነው የተናገሩት።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም