ከከሰል ጋር ተመሳስሎ አውሮፓ እንዲገባ የተዘጋጀው ኮኬይን ተያዘ

146

ሐምሌ 9 ቀን 2013 (ኢዜአ) ከ41 ሚሊየን ዶላር በላይ ግምት ያለውና ከከሰል ጋር ተመሳስሎ አውሮፓ እንዲገባ የተዘጋጀው ኮኬይን የተባለ አደንዛዥ እጽ መያዙን የአየርላንድና ሆላንድ ደህንነት ባለስልጣናት ይፋ አድርገዋል።

መነሻውን ደቡብ አሜሪካ በማድረግ በሁለት እቃ ጫኝ መርከቦች ተጓጉዞ ሆላንድ ሮተርዳም ወደብ የደረሰው ኮኬይኑ የአየርላንድ የደህንነት ሰዎች ከነበራቸው ጥርጣሬ በመነሳት ምርመራ ማድረጋቸውን ተከትሎ መገኘቱን የአየርላንድ ፖሊስና ደህንነት አገልግሎት ገልጿል።

ለኤክስ ሬይ ማሽኖችና ለፖሊስ አነፍናፊ ውሾች ምስጋና ይድረስና ኮኬይኖቹ በ2ሺህ ከረጢቶች ከከሰል ጋር ተደባልቀው ተሞልተው የተገኙ ሲሆን ከሰሉን ከኮይኑ ለመለየት ቀናት እንደሚወስድ የአየርላንግ ፎረንሲክ ሳይንስ መስሪያ ቤት መናገራቸውን ሲኤን ኤን ዘግቧል።

ኮኬይኑ የተጫነበት መርከብ ሮተርዳም የደረሰው ከሳምንት በፊት ሲሆን ምርመራው እንደተጠናቀቀ የመርከቡ ሰራተኞች ወደ እስርቤት ይላካሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው አስነብቧል።

የምርመራ ውጤቱ የተደራጀ ወንጀልና የአደንዛዥ እጾች ዝውውር ውስጥ ያሉና ኑሮዋቸውን በአየርላንድ ያደረጉ ሰዎችን ለመልቀም የሚያስችል መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን የሃገሪቱ ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነር ጆን ኦድሪስኮል መናገራቸውም ተገልጿል።

ፖሊስ ረዳት ኮሚሽነሩ ሃሳባቸውን ሲቀጥሉ ተመሳሳይ ወንጀሎችን ለመከላከልና በአውሮፓ ማህበረሰብ ዘንድም ተገቢው የህግ ማስከበር እንዲኖር ካስፈለገ አለም አቀፍ ትብብር ማድረጉ ወሳኝ ነው ብለዋል።

ክስተቱ የአውሮፓ ህብረት በተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ላይ ሊወሰድ ስለሚገባው አስፈላጊ የመከላከልና የማስወገድ እርምጃ እንዲያስብበት ለማድረግ መነሻ ሊሆነው እንደሚችል ያስነበበው ዘገባው ተመሳሳይ ክስተቶች በአውሮፓ እየተደጋገሙ መምጣታቸውን ስፔንን ለማሳያነት አቅርቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም