የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የፎሪንሲክ ምርመራ ጀመረ

106
አዲስ አበባ ነሃሴ 1/2010 የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የፎሪንሲክ ምርመራ አገልግሎት ጀመረ። ምርመራው የሚካሄድበት ማዕከል ግንባታ በ26 ሚሊዮን ብር ወጪ መከናወኑንም ነው ኮሌጁ ለኢዜአ የገለጸው። ምርመራውን የሚያግዙ መሳሪያዎች ደግሞ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገዝተዋል። የህክምና አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ለመስጠትም ለህክምና ባለሙያዎች ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ኮሌጁ ገልጿል። የፎሬንሲክ ምርመራ የአስክሬን፣ የወላጅነት ማረጋገጫ የዘረመል/ዲ ኤን ኤ/፣ የስነ ምረዛ ምርመራዎችንና በጥይትና በስለታማ ቁሶች የሚከሰት አደጋንም ጭምር በምርመራ ማረጋገጥ የሚያስችል የምርመራ አይነት ነው። የሆስፒታሉ የህክምና ዘርፍ ምክትል ፕሮቮስት ዶክተር ብርሃኔ ረዳኢ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ይሰጥ የነበረው የፎሬንሲክ ምርመራ የአስክሬን ምርመራ ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል። የአስክሬን ምርመራውም ቢሆን ከውጭ በሚመጡ ባለሙያዎች ብቻ እንደሚሰጥ በመጠቆም አሰራሩ በህግ፣ በትርጉም፣ በቋንቋና በባህል ከፍተኛ ጫናና አለመግባባት ሲፈጥር ቆይቷል ብለዋል። ሆስፒታሉ በአሁኑ ወቅት በፎረንሲክ ምርመራ ስር ያሉ ሁሉንም የምርመራ አይነቶችን በአገር ውስጥ ለመስጠት በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ ማዕከል ገንብቶና ለምርመራው የሚያስፈልጉ መሳሪያዎችን ገዝቶ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል። በተጨማሪም ምርመራውን በአገር ውስጥ ባለሙያዎች ለመስጠት ለሙያተኞች የፎረንሲክ ምርመራ ስልጠና እየተሰጣቸው እንደሚገኝም ዶክተር ብርሃኔ አክለዋል። ቀደም ሲል በፎረንሲክ ምርመራ የሚረጋገጡ ናሙናዎችን ወደ ውጭ በመላክ ውጤቱ እስኪመጣ የሚጠበቀውን ጊዜና እንግልት ከማስቀረቱም በላይ አገሪቱ በጤናው ዘርፍ እያመጣች ላለው ለውጥ ትልቁን ድርሻ እንደሚወስድ አመልክተዋል። በሆስፒታሉ የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ፕሮቮስት አቶ ባልካቸው ንጋቱ በበኩላቸው የፎረንሲክ ምርመራ በአገር ውስጥ ሃኪሞች ብቻ እንዲሰጥ በዘርፉ የተሰማሩ ሃኪሞች ስልጠና ከጀመሩ ሁለት ዓመት ሆኗቸዋል ብለዋል። ስልጠናውን እየወሰዱ የሚገኙ ሃኪሞች ለሶስት ወራት የሚቆይ የልምድ ልውውጥ እንዲኖራቸውና አቅማቸውን እንዲገነቡ ለማስቻልም ሆስፒታሉ ከህንድና ከተለያዩ አገራት ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል ይላሉ። ይህም ዓለም የደረሰበት የፎሬንሲክ ምርመራ ኢትዮጵያ ውስጥም ተግባራዊ እንዲሆን የልምድ ልውውጡ ያለው ሚና ጉልህ ነው ሲሉም አብራርተዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም