የምግብ ሥርዓት መዋቅራዊ ለውጥ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ

94

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 8 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከምርት እስከ አመጋገብ ድረስ ትኩረት የሚያደርግ ለ10 ዓመታት ተግባራዊ የሚሆን የምግብ ሥርዓት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ የዘላቂ ልማት ግቦች የ10 ዓመት የትግበራ አካል የሆነውን የምግብ ሥርዓት ጉባኤ በመጪው መስከረም 2014 ዓ.ም ያካሂዳል።  

ጉባኤው የአገራት በምግብ ሥርዓት መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት ትልቅ ግብዓት እንደሚሆንና የትግበራ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ታምኖበታል።

ኢትዮጵያም የራሷን ነባራዊ ሁኔታና ዘላቂ የልማት ግቦችን ከግምት ያስገባ "የኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓት መዋቅራዊ ለውጥ" የተሰኘ አገር በቀል ፍኖተ ካርታ አዘጋጅታለች።

ፍኖተ ካርታውም ተ.መ.ድ በቀጣይ ዓመት በመስከርም በሚያደርገው ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ የዘርፉ አቅጣጫ ሆኖ እንደሚቀርብ ነው የግብርና ሚኒስትር አቶ ኡመር ሁሴን የተናገሩት።

ፍኖተ ካርታው ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች የዘርፉን ችግሮችና መልካም እድሎች አስገብቶ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዋናነትም የምርት ሂደትን፣ በማቀነባበር፣ በትራንስፖርትና በአመጋገብ ላይ ትኩረት በማድረግ የእሴት ሰንሰለቱን ተከትሎ የተዘጋጀ ሁሉን አቀፍ ፍኖተ ካርታ መሆኑን ነው ያነሱት።  

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው፤ ፍኖተ ካርታው በጤናው ዘርፍ በተለይም ከሥርዓተ- ምግብ ጋር በተያያዘ ችግሮችን ለማቃለል እንደሚረዳ ጠቁመዋል።

ያም ብቻ ሳይሆን አሁን አሁን ከአመጋገብ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ እንደ ደም ብዛትና ስኳር ያሉ የጤና እክሎችንም ለመከላከል ሁነኛ መፍትሄ ማካተቱን ተናግረዋል።

እነዚህንና ሌሎችም የጤና ችግሮችን ሁሉን አቀፍ ምላሽ ለመስጠት ያስችላል ያሉት የጤና ሚኒስትሯ፤ ፍኖተ ካርታው አዳዲስ ግቦችንም ጭምር የያዘ መሆኑን አስረድተዋል።

ፍኖተ ካርታው በተ.መ.ድ ጉባኤ ቀርቦ ይሁንታ ከተገኘ በኋላ የሃብት ማሰባሰብ ተካሂዶ ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል እቅድ እንደሚወጣ ጠቁመዋል።

ፍኖተ ካርታው በዋነኝነት ሁሉም የሥርዓተ-ምግብ ተዋናዮች ተሳትፎውን ባረጋገጠ መልኩ ጠንካራ፣ ዘላቂና ተጠያቂነት ያለው የሥርዓተ-ምግብ ለውጥ ለማምጣተ ትኩረት ያደርጋል።

በተለይም የግብርና ቴክኖሎጂዎች ኢኖቬሽንና ግብዓቶች ቅርቦት በማሳደግ፣ ምርትና ምርታማነትን ለመጨመርና የገበያ መረጃ መሠረተ ልማት ተደራሽነት ለማጠናከርም ዓላም አድርጓል።

ጎን ለጎንም የምግብ እሴት ሰንሰለትን ማጠናከር፣ ጤናማ ምግብን መሠረት ያደረገ የአመጋገብ መመሪያና የሥርዓተ ምግብ ትምህርት ማስተዋወቅ ላይ ትኩረት ያደርጋል ተብሏል።

በዘርፉ የተናበበ የመሬት ሪፎርም ፖሊሲ እንዲጠናከርና ለግብርናና ገጠር መዋቅራዊ ለውጥ የመንግሥት የፋይናንስ ድጋፋ ለማጠናከርም አልሟል።

በተጓዳኝም አደጋ መከላከልና ተጋላጭነት መቀነስም ላይ ፍኖተ ካርታው ትኩረት እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም