ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን በዘላቂነት ለመከላከል ወቅቱን የሚመጥን የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ ጥናት አመለከተ

190

ሐምሌ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በዘላቂነት ለመከላከል ወቅቱን የሚመጥን የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንደሚያስፈልግ በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት የተካሄደ አንድ ጥናት አመለከተ።

ሦስተኛው አገር አቀፍ የፖሊስ ጥናት ሲምፖዚየም በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት በሰንዳፋ እየተካሄደ ይገኛል።

ከቀረቡት ጥናቶች መካከል አንዱ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣውን ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን መከላከል በሚቻልበት ዙሪያ የተደረገ ነው።

የጥናቱ አቅራቢ ኢንስፔክተር አብዱልፈታ ኢድሪስ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መስፋፋት ከዜናነት ባለፈ የዝውውር መንገዱ ሊታወቅ እንደሚገባ አመልክተዋል።

በጥናት ግኝቱም የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎቹ እጅግ የረቀቀ የማዘዋወሪያ መንገድ እየተጠቀሙ መሆኑን መረጋገጡን ጠቁመዋል።

በተሽከርካሪ ከተጫኑ የቁም ከብቶች መካከል አንዱን ስጋውን አውጥተው በከብቱ ሆድ እቃ መሳሪያ እስከ መደበቅ የደረሱ አካሄዶች መኖራቸውንም ለአብነት አንስተዋል።

''ለዚህም ነው አንድ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ከድንበር ተነስቶ ሰባት ስምንት ኬላ አልፎ አዲስ አበባ የሚደርሰው'' ብለዋል።

ችግሩን ለመከላከል ዘመኑን የሚመጥን ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መከላከያ መንደፍ ላይ ማተኮር አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

“እነዚህ የጥናት ውጤቶች በተቻለ መጠን ተግባራዊ እንዲደረጉ ይሰራል” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የጥናትና ምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ሲሳይ ዘለቀ ናቸው።

በኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ማማከርና የሕብረተሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ረዳት ኮሚሽነር ተሻለ ተሾመ “በሲምፖዚየሙ የፖሊስ አገልግሎትን የሚያሻሽሉ የጥናት ውጤቶች ይቀርባሉ” ብለዋል።

በሲምፖዚየሙ ሁለት ቀናት ቆይታ በሰላምና ደህንነት፣ በወንጀል ምርመራ ዙሪያ፣ በፎረንሲክ ሳይንስ እንዲሁም በፖሊስ አስተዳደርና መሪነት ላይ ያተኮሩ 15 የጥናት ውጤቶች እንደሚቀርቡ ተጠቁሟል።

የጥናት መስኮቹ የተመረጡትም የፖሊሳዊ አገልግሎት ጉድለቶችን መነሻ አድርጎ እንደሆነም ተናግረዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ጄነራልና የፖሊስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት መስፈን አበበ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የፖሊስ አገልግሎትን በጥናትና ምርምር የማዘመን ሥራ ይሰራል።

በሕግ ማስከበርና በተልዕኮ አፈጻጸም ላይ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን ጠቅሰው፤ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት አክብሮ ከመሥራትና በሌሎች ፖሊሳዊ አገልግሎቶች ላይ መፈተሽ የሚገባቸው በርካታ ነገሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

እነዚህን አገልግሎቶች ለማሻሻል ደግሞ በዘርፉ ላይ ያተኮሩ ጥናትና ምርምሮች በስፋት መሰራትና መፍትሔ ማመላከት አለባቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም