በመተከል ዞን የሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የመጣው ሰላም ምልክት ነው - ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ

161

ሐምሌ 08 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአካባቢው ለመጣው ሰላም አንድ ምልክት ተደርጎ እንደሚወሰድ የምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥና የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ኃይል ኮማንድ ፖስት አባል ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ ገለጹ።

ሦስተኛው ዙር "ኢትዮጵያን እናልብሳት" የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በመላ አገሪቷ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የዚሁ አካል የሆነው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር የመተከል ዞን ኮማንድ ፖስት፣ የዞን፣ የወረዳ እና የሰባተኛ መካናይዝድ ክፍለ ጦር አመራርና አባላት በተሳተፉበት በፓዊ ወረዳ ተካሂዷል።

ብርጋዴር ጄኔራል አለማየሁ ወልዴ እንደተናገሩት፤ ሠራዊቱ የአገርን ዳር ድንበር ከመጠበቅና የህዝብን ደህንነት ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በልማት ስራዎች እየተሳተፈ ይገኛል።

ኮማንድ ፖስቱና ሠራዊቱ ባከናወኗቸው ተግባራት በመተከል ዞን ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት በማስቆም አንጻራዊ ሰላም ለማስፈን መቻሉን ገልጸዋል።

በዚህም በተለያዩ ወረዳዎች እየተካሄደ ያለው "ኢትዮጵያን እናልብሳት" የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዞኑ ለመጣው ሰላም አንዱ ምልክት ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን ተናግረዋል።

የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ በበኩላቸው ሠራዊቱ የዞኑን ሰላም ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ካሉ ተግባራት በተጨማሪ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ችግኞች በመትከል የልማት አጋርነቱን በማሳየቱ ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ ክልልን በመወከል የኮማንድ ፖስቱ አባል የሆኑት አቶ አጀበ ስንሻው፤ ሁሉም አካል በአረንጓዴ አሻራ መሳተፍ እንዳለበት ገልጸዋል።

ሠራዊቱ ሰላምና ደህንነትን ከማረጋገጥ ጎን ለጎን በልማት ስራዎች መሳተፉ የህዝብ ወገንተኝነቱ ማረጋገጫ መሆኑን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም