ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሱዳን መንግስት ባለስልጣናት ጋር ተወያዩ

101
አዲስ አበባ ሐምሌ 30/2010 የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሱዳን መንግስት ባለስልጣናት ጋር ካርቱም ውስጥ ተወያዩ። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሱዳን የተገኙት የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት /ኢጋድ/ አባል አገራት መሪዎች በሱዳን ካርቱም የደቡብ ሱዳን የሰላምና የአንድነት ስምምነት ለመቋጨት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ለመገኘት ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚሁ መድረክ ጎን ፕሬዝዳንት ኦመር ሀሰን አልበሽርን ጨምሮ ከሱዳን መንግስት ባለስልጣናት ጋር መወያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፅህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል። አቶ ደመቀ ከሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽር፣ ከምክትል ፕሬዝዳንት ሃሳቦ ሞሀመድ እና ከብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር ዶክተር ፋይሳል ሐሰን ጋር በሁለትዮሽ እና በአካባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ጊዜ የደቡብ ሱዳን ሰላም ሂደት እንዲሳካ የሱዳን መንግስት ያደረገውን አስተዋጽኦን አድንቀዋል። በውይይቱ ወቅትም አቶ ደመቀ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮችና በኢትዮ-ኤርትራ የሰላም ስምምነት ዙሪያ ለሱዳን ባለስልጣናት ገለጻ አድርገዋል። የሱዳን መንግስት 1 ሺህ 400 ኢትዮጵያዊያንን ከእስር በመፍታቱ እና የህዳሴው ግድብ ፕሮጀክትን በተመለከተ ላሳየው የማይናወጥ አቋም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ ምስጋና አቅርበዋል። የሱዳን ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እየወሰዱ ያለውን የተለያየ እርምጃ በማድነቅ ከኤርትራ ጋር የተጀመረው ዕርቅ ለአካበቢው ሠላምና መረጋጋት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸዋል። በኢትዮ-ሱዳን ድንበር አካባቢ አልፎ አልፎ የሚከሰተው ግጭት በሠላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበት ፕሬዝዳንት ኦማር ሀሰን አልበሽር ተናግረዋል። የደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በዋና ዋና ጉዳዮች ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረሳቸው አበረታች ነው ያሉት አቶ ደመቀ ሁሉም ኃይሎች ስምምነቱን እንዲተገብሩ ጥሪ አቅርበዋል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ግንባር ቀደም የዕፅዋት ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው የእንግሊዝ ሮያል ሶሳይቲ አባል ሆነው መመረጣቸውን ጽሀፍት ቤቱ አስታውቋል። ሮያል ሶሳይቲ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በሳይንስ ዘርፍ ታላቅ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ግለሰቦችን አወዳድሮ በየዓመቱ የአባልነት መብትና እውቅና የሚሰጥ በእንግሊዝ የሚገኝ መንግስታዊ ያልሆነ የጥናትና ምርምር ተቋም ነው። ፕሮፌሰሩን ለእውቅና ያበቃቸው በኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ዙሪያ ለረዥም ጊዜ ጥልቅ ጥናትና ምርምር ማድረጋቸው፣ አገሪቱ ከዘርፉ ተጠቃሚ እንድትሆን እንዲሁም ዘርፉ በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ያከናወኑት የላቀ ተግባር መሆኑን ማህበሩ ገልጿል። ፕሮፌሰሩ የማህበሩ አባል መሆናቸው፣ አገራችን ውስጥ የሚገኙ የምርምርና የጥናት ተቋማት እንዲሁም የመንግስት መስሪያ ቤቶች ከሮያል ሶሳይቲ ጋር ግንኙነት በመፍጠር የእውቀትና ክህሎት ሽግግር እንዲደረግ የማገዝ እድል ይፈጥርላቸዋል ተብሏል። ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው ፣ በማህበሩ የ357 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ማህበሩን የተቀላቀሉ የመጀመሪያው ከሰሀራ በታች የሚገኙ አፍሪካዊ ሳይንቲስት መሆናቸው ተገልጿል። በተመሳሳይ ባለፈው ዓመት ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ የተባለ የእንግሊዝ ተቋም ዓለም ዓቀፍ ሽልማት ለፕሮፌሰር ሰብስቤ ማበርከቱ ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም