በኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት የቴክኖሎጂ ሽግግር መፍጠር እንፈልጋለን - የቼክ ሪፐብሊክ ባለሃብቶች

86
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2010 በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት የቴክኖሎጂ ሽግግር መፍጠር እንደሚፈልጉ የቼክ ሪፐብሊክ ባለባብቶች ገለጹ። ባለሃብቶቹ በመድሃኒት አቅርቦት፣ በአየር ትራፊክ ቁጥጥር፣ በግብርና፣ በኮንስትራክሽንና በኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች መሰማራት የሚፈልጉ ናቸው። የቼክ የኮንስትራክሽን ግብዓት አምራች ካምፓኒ ሶማቲ ሲስተም ኤስ.አር.ኦ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጂሪ ሩክ ለኢዜአ እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ ያለውን የኮንስትራክሽን ዘርፍ በመጠቀም የተለያዩ የግንባታ ቁሳቁሶችን የማቅረብ ፍላጎት አላቸው። በአውሮፓ፣ በአሜሪካና በኤዥያ ባሉ አገሮች ያላቸውን የካበተ ልምድ በመጠቀም ደረጃውን የጠበቀ የእሳት አደጋ ጊዜ መውጫ መሳሪያዎችን ወደ ኢትዮጵያ ማምጣት ይፈልጋሉ። በአገሪቱ በስፋት እየተከናወነ ያለውን የግንባታ ዘርፍ በመጠቀም ምርቶቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት ከተለያዩ የመንግስት አካላትና ባለሃብቶች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑንም አስረድተዋል። ይኸውም በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በማሳደግ፣ የግል ባለሃብቱን በማነሳሳትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር ሚናው የጎላ እንደሚሆን ጠቁመዋል። የኮም አፕ (ኮምቲውተር አፕሊኬሽን) ካምፓኒ የሽያጭ ማናጀር ሉካስ ቫጅነር በበኩላቸው 'ምርቶቻችንን በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ስናስተዋውቅ ብንቆይም ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ነው' ብለዋል። በቆይታቸውም ከኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች ጋር በመነጋገር ምርቶቻቸውን ለማቅረብ ቅድመ ሁኔታዎችን እያመቻቹ መሆኑን አስረድተዋል። የግል ባለሃብቶች ተቀራርበው መስራት የሚችሉበት እድል መመቻቸቱም በሁለቱን አገሮች መካከል ያለውን የንግድና ኢንቨስመንት እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃ ጠቁመዋል። የኮንስትራክሽንና ኤሌክትሪካል እቃዎች አቅራቢ የሙያቡ ትሬዲንግ ስራ አስኪያጅ ወጣት ሙባረክ ቢያ የቼክ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለደንበኞች አማራጭ ምርቶችን ለማቅረብ እንደሚያግዝ አስረድቷል። "አለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ከሆኑ ከቼክ ካምፓኒዎች ጋር ተቀራርበን መወያየታችን ያሉብንን ክፍተቶች ለመሙላት ያግዘናል" ነው ያለው። 'በቀጣይም አቅማችንን በማጠናከር አምራች ድርጅቶች ለመሆን በምናደርገው እንቅስቃሴ እንደ ግብዓት የሚያገለግሉ ጠቃሚ ሃሳቦችን አግኝተናል' ብሏል። በአዲስ አበባ በተካሄደው የኢትዮ- ቼክ ቢዝነስ ፎረም ከኮም አፕና ሶማቲ ሲስተም በተጨማሪ በአየር ትራፊክ ቁጥጥር ላይ የሚሰራው ትራንስኮን ኤሌክትሮኒክስ ሲስተምና ሌሎችም ካምፓኒዎች ስራቸውን አስተዋውቀዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም