የወሰን ተሻጋሪ በጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብር ነገ በይፋ ይጀመራል

66
አዲስ አበባ ሐምሌ 30/2010 በኢትዮጵያ የወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብር ከነገ ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም ጀምሮ በሀገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ እንደሚሆን የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ። በሚኒስቴሩ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ናስር ለገሰ ለኢዜአ እንደገለጹት  ከነገ ጀምሮ ለአስር ተከታታይ ቀናት በሚቆየውና የአንድ ክልል ወጣቶች ወደሌላው ክልል በመጓዝ በሚከናወነው የበጎ ፍቃድ መርሃ-ግብር ላይ ለመሳተፍ አንድ ሺህ ያህል ወጣቶች ተመዝግበዋል። በአንዱ ክልል ያለው ወጣት ወደሌሎች የተለያዩ ክልሎች ተጉዞ  በበጎ ፍቃደኝነት አገልግሎት መስጠቱ በሀገሪቱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎትን ለማሳደግ የሚያስችል ንቅናቄ ለመፍጠር እንደሚያግዝ ዳይሬክተሩ ገልፀዋል። ከዚህ በላይ ግን በክልሎች መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር እና የአንድነትና የፍቅር ተምሳሌት በመሆን ማህበራዊ ትስስርን ለመፍጠርም ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው ነው ዳይሬክተሩ የተናገሩት። መርሃ-ግብሩ ለአገር ገጽታ ግንባታም አዎንታዊ አመለካከትን ከማዳበር አንጻር የሚኖረው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን አመልክተዋል። በወሰን ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ መርሃ-ግብር መሰረት ወደ ተለያዩ ክልሎች የሚሰማሩት ወጣቶች በነገው ዕለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎም ይጠበቃል። ከወሰን ተሻጋሪው በጎ ፈቃድ ሌላ እየተጠናቀቀ ባለው የ2010 ዓ.ም በጋ ወቅት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ላይ 12 ነጥብ 7 ሚሊዮን ወጣቶች ተሳትፈዋል። በተያዘው ክረምት ወቅት ደግሞ 13 ነጥብ 6 ሚሊዮን ወጣቶች በአገር አቀፍ ደረጃ በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ለመሰማራት መመዝገባቸውን ጠቅሰዋል። እነዚህን ወጣቶች ወደ ስራ ለማሰማራት 14 የስራ መስኮች የተለዩ ሲሆን ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመሆን የዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል። ከነዚህም ውስጥ የደም ልገሳ፣ ትምህርት ቤቶች አካባቢ የትራፊክ ማስተባበር፣ የልምድ ማካፈልና የማስተማር እንዲሁም የግብርና ስራዎችን ጠቅሰዋል። የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሀብት ብክነትን ከማስወገድ፣ የጎርፍና የትራፊክ አደጋን ከመከላከል ብሎም በደም እጥረት ምክንያት የሚጠፋውን ህይወት ከማዳን አንጻር ያለው ጠቀሜታ በዋጋ አይተመንም። እንዲያም ሆኖ በተያዘው ክረምት በተለያየ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የሚሰማሩት ወጣቶች ተግባር በገንዘብ ቢተመን በትንሹ ከ20 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚሆን ተናገረዋል። የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከወጣቶች ባሻገር በማንኛውም ዕድሜ የሚገኙ ዜጎችን ያካተተ እንዲሆን ለማድረግ በአገር አቀፍ ደረጃ ረቂቅ የፖሊሲ ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል። ረቂቅ ፖሊሲው የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በመውሰድ ከመንግስትና ከግል ስራዎች ጡረታ የወጡ ዜጎች፣ ባለኃብቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማሳተፍ የሚያስችል ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም