ሚኒስትሯ በሐረሪ ክልል እየተከናወኑ ያሉ አቅመ ደካማ ወገኖች የቤት እድሳት ሥራዎችን አበረታቱ

46

ሐረር ፤ሐምሌ2/2013(ኢዜአ) በሐረሪ ክልል በሰላም ቤተሰቦችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እየተከናወኑ ያሉ አቅመ ደካማ ወገኖችን የቤት እድሳትና ጥገና ሥራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።

ሚኒስትሯ በሥፍራው ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት እንዳመለከቱት፤ በክልሉ የሰላም ቤተሰቦችና በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች እያከናወናቸው የሚገኙ የበጎ አድራጎት ሥራዎች መጠናከር አለባቸው።

ወጣቶቹ በሐረር ከተማ አሚር ኑር፣ ጅኔላና ሐኪም ወረዳዎች ላይ እያከናወኑ የሚገኙትን የቤት ግንባታ ጥገናና እድሳት ሥራዎች የሚበረታቱና ለአቅመ ደካሞች እፎይታን የሚሰጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የሰላም ግንባታ ሥራዎችን ጨምሮ ሌሎችንም የበጎ አድራጎት ልምዳቸውን ለሌሎች እንዲያካፍሉ ጠቁመዋል።

ሚንስትሯ በተለይ በአባድር ወረዳ የሚገኙ ህጻናት የወጣቶቹን በጎ ተግባር በመቅሰም በትምህርታቸው ጠንካራ እንዲሆኑና አረጋውያንን እና አቅመ ደካሞችን የሚያግዙ እንዲሆኑ መክረዋል።

በከተማው ቀበሌ 14 በተለምዶ ቡቴ በሚባለው አካባቢ የሚገኘውን የሰላም ቤተሰብ መኖሪያ ቤትንና  የከተማው ወጣቶች በፈቃደኝነት የሚያከናውኑ የምሽት ጥበቃ /ሮንድ/ ሥራም ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ስነ-ስርዓት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ፣ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ሚኒስትሯ ዛሬ ከሰላም ቤተሰቦችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ወይዘሮ ሙፊሪያት ቀደም ሲል በድሬዳዋ አስተዳደር ጉብኝት ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በወቅቱ ዘግቧል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም