የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት ተግባራዊነት ላይ የሚመክር ስብሰባ በቀጣይ ሳምንት ይካሄዳል

57
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2010 የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት ተግባራዊነት ላይ የሚመክር የሚኒስትሮች ስብሰባ በቀጣይ ሳምንት በቶጎ ርዕሰ መዲና ሎሜ ከግንቦት 17 እስከ 20 ቀን 2010 ዓ.ም ይካሄዳል። ጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም በአዲስ አበባ 30ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሲካሄድ ኢትዮጵያን ጨምሮ 25 አገሮች የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት መፈረማቸው ይታወቃል። በጉባኤው ላይ የአገሮቹ መሪዎች ለስምምነቱ መነሻ የሆነው የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ለማቋቋም መሰረት የጣለውንና እ.አ.አ በ1999 በኮትዲቭዋር የተፈረመውን የያሙሱክሮ ድንጋጌ ማጽደቃቸው ይታወሳል። አገሮቹ የፈረሙት ስምምነት ከዚህ ቀደም በአህጉሩ የአንድ አገር አየር መንገድ ወደ ሌላ አገር ለመብረር ፍቃድ መጠየቅ ያስፈልግ የነበረውን አሰራር በማስቀረት ያለምንም ገደብ ወደ የትኛውም የአፍሪካ አገር ለመብረር የሚያስችል እንደሆነ በወቅቱ ተገልጾ ነበር። ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው የሚኒስትሮች ስብሰባ አገሮቹ የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነትን ይፋ ካደረጉ በኋላ የመጀመሪያው መሆኑን የአፍሪካ ህብረት አስታውቋል። ስብሰባው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽንና በቶጎ መንግስት በጋራ የሚዘጋጅ ነው። የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት የፈረሙ አገሮች መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ስምምነቶች በማቀናጀትና በማዋሀድ ስምምነቱ በፍጥነት ወደ ትግበራ ማስገባት የስብስባው ዋንኛ አላማ እንደሆነ ተገልጿል። በስብሰባው ላይ የሚፈረሙትን የጋራ መግባቢያ ሰነዶችና የሁለትዮሽ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ስምምነቶች የሚፈርሙ የሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ወይም በአቪዬሽን ዘርፉ ላይ የሚሰራ የስራ ሃላፊ አገሮቻቸውን መወከል እንዳለባቸው ተጠቁሟል። የሚወከለው የአቪዬሽን ዘርፉ የስራ ሃላፊ በአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት ላይ የሚደረጉ ስምምነቶችን ለመፈረምና ለመደራደር ህጋዊ እውቅና የተሰጠው እንደሚገባም የአፍሪካ ህብረት ገልጿል። የአፍሪካ ሲቪል አቪዬሽን ኮሚሽን በያሙሱክሮ ድንጋጌ በውድድርና በደንበኞች ጥበቃ የተቀመጡትን ደንቦች ለአገሮቹ እንደሚያሰራጭ ተነግሯል። የሚኒስትሮቹ ስብሰባ ግንቦት 20 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካሄድ ሲሆን ከዛ ቀደም ብሎ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ስብስባ ከግንቦት 17 እስክ 19 ቀን 2010 ዓ.ም እንደሚካሄድ የወጣው መርሃ ግብር ያመለክታል። የአፍሪካ ነጻ የአየር ትራንስፖርት ገበያ ስምምነት መፈረም የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካ ህብረት ጋር ሲሰራ እንደነበር ይታወሳል። አፍሪካ የአየር ትራንስፖርት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ በንግድ፣ ኢኮኖሚ፣ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፎች የሚጠበቀውን ያህል መተሳሰር ያለመቻሉን ባለሙያዎች ይገልጻሉ።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም