በሰሜን ወሎ ዞን ከ57ሺ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ወሎ ዞን ከ57ሺ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል ተፈጥሯል
76
ወልድያ ሃምሌ 30/2010 በሰሜን ወሎ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ57ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች የስራ እድል መፈጠሩን የዞኑ የቴክኒክና ሙያ መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የግንዛቤ ፈጠራና የሥራ እድል ባለሙያ አቶ በየነ ሲሳይ እንዳሉት የስራ እድሉ የተፈጠረው በዞኑ በሚገኙ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ነው። የስራ እድል የተፈጠረውም በእንጨትና ብረታብረት ስራ፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በብሎኬት ማምረት፣ በንግድና አገልግሎት፣ በልብስ ስፌት፣ ምግብ ዝግጅትና ሌሎች ተያያዝ ዘርፎች ነው። ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) የተገኘ 195 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በብድር መሰራጨቱን ጠቁመው የመስሪያ ቦታ፣ አጫጭር ስልጠናና ሌሎች ድጋፎች እንደተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡ ባገኙት የ646ሺ ብር ብድር ማሽኖችንና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ገዝተው ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ወደ ስራ መግባታቸውን የገለፀው ደግሞ የእነ ተስፋዬ፣ ሙሉጌታና ጓደኞቻቸው ማህበር ገንዘብ ያዢ ወጣት ተስፋየ ሞላ ገልጿል። ማህበራቸው አምስት አባላት ያሉት ሲሆን ባገኙት የብድርና ሌሎች ድጋፎች ተጠቅመው የማሽን መለዋወጫዎችን በማምረት ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸውን ተናግሯል። የመረጡት የስራ ዘርፍ አዋጭ በመሆኑ በየወሩ 14ሺህ600 ብር ብድር እየከፈሉ መሆኑን አመልክተዋል። እነ ፍሬው፣ መንገሻና ጓደኞቻቸው የእንጨትና ብረታብረት ስራ ማህበር ጸሐፊ ወጣት መንገሻ ይመር በበኩሉ ማህበራቸው በተመሳሰይ ሙያ ተቀጥረው ሲሰሩ የነበሩ ሶስት አባላት ያሉት ነው። አባላቱ ባዋጡት 35ሺህ ብር የእንጨት ማሽን የገዙ ሲሆን የመስሪያ ቦታ ከአካበቢው መስተዳድር ወስደው የእንጨትና ብረታብረት ውጤቶችን በማምረት ለአካባቢው ህብረተሰብ አገልገሎት እየሰጡ ይገኛሉ። እነተስፋዬ፣ ዳንኤልና ጓደኞቻቸው ዳቦ መጋገሪያ ማህበር ኃላፊ ወጣት ተስፋየ አየነ እንዳለው በተሰጣቸው 25ሺህ ብር ብድር ሁለት የዳቦ መጋገሪያ ማሽን ገዝተውና የግለሰብ ቤት ተከራይተው በዳቦ ማምረት ስራ መሰማራተቸውን ተናግሯል።