የአገር ውስጥ የሎጂስቲክ አፈጻጸም ደረጃ ጠቋሚ ሰነድ ይፋ ሆነ

75

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 29/2013 (ኢዜአ) የአገር ውስጥ የሎጂስቲክ አፈጻጸም ደረጃ ጠቋሚ ሰነድ ይፋ ሆነ።

ኢትዮጵያ በሎጂስቲክ አፈጻጸም ከዓለም አሁን ካለችበት 126ኛ ደረጃ በአስር ዓመት ወስጥ 40ኛ ላይ ለማድረስ ታቅዷል።

ዘላቂነት ያለው የመረጃ ሥርዓት በዘርፉ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉም ጥሪ ቀርቧል። 

በአገር ውስጥ ባለሙያዎች የተዘጋጀው የአገር ውስጥ የሎጂስቲክ አፈጻጸም ደረጃ ጠቋሚ ቀመር ሰነድ ይፋ ሆኗል፤ መሰል ሰነድ በየዓመቱ እንደሚዘጋጅም ታውቋል።

በሰነዱ በሎጂስቲክ ዘርፉ የተዘጋጀና ከ300 በላይ ሰዎችን ያሳተፈ ጥናት ተካሂዶ በዘርፉ ያሉ ችግሮችና ጥንካሬዎችን እንዲሁም ምክረ-ሐሳቦችን ያካተተ ነው።

ሰነዱን ያቀረቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሎጂስቲክ መምህርና የሎጂስቲክ ትራንስፎርሜሽን ጽህፈት ቤት አማካሪ ዶክተር ማቴዎስ ኢንሰርሙ እንዳሉት፤ የዓለም ባንክ በየሁለት ዓመቱ የሎጂስቲክ ዘርፍን የሚለካበትን ስድስት መለኪያዎችን በመጠቀም ነው ጥናቱ የተጠናው።

የጉምሩክ ሂደት ውጤታማነት፣ ጊዜ፣ መሠረተልማትና የአገልግሎት ሰጪዎች ብቃትና ቅልጥፍናም ከመለኪያዎቹ መካከል ናቸው።

በእነዚህ መለኪያዎች መሠረትም አገሪቱ በአጠቃላይ በአማካይ ከአምስት፤ 2 ነጥብ 51 መሆኑን አስረድተው ይህም በ2014 ከነበረው ከፍተኛ 2 ነጥብ 59 ቀጥሎ የተሻለ መሆኑን አስረድተዋል።

የሎጂስቲክ አፈጻጸም መለኪያ በራስ አቅም ተጠንቶ መጠቀም ሊጀመር መሆኑ በዘርፉ ትርጉም ያለው ለውጥ ለማምጣት ያስችላል ያሉት ደግሞ የትራንስፖርት ሚንስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ናቸው።

በዘርፉ ያለን ጥንካሬና ድክመት ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ እየተመዘነና እየተለየ ሎጂስቲኩን ሊያሰራ ያላስቻለውን ማነቆ ለመፍታት እድል እንደሚሰጥ አስረድተዋል።

በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት በሎጂስቲክ አፈጻጸም አገሪቱ ይኖራታል ተብሎ የታቀደውን ደረጃ ለማሳካት ያስችላል።

ኢትዮጵያ በ2016 በሎጂስቲክ አፈጻጸም ከዓለም 126ኛ ደረጃ እንደነበረች አስታውሰው በአሥር ዓመቱ መሪ እቅድ ደረጃዋን ወደ 40ኛ ለማድረስ መታቀዱን አብራርተዋል።

ወደዚህ ደረጃ ለመድረስ እየተለካና የጎደለው እየተሞላ መሄድ እንደሚገባ ገልጸው ሰነዱ አገር ውስጥ ያለውን እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን የውጭ ባለሃብቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ እድል የሚሰጥ ነው ብለዋል።

መሠረተ ልማትና የተቋማት አቅም ግንባታ ላይ ሊሰራ  እንደሚገባ ሪፖርቱ በማመላከቱ ይህንን በእቅድ በማካተት ይሰራልም ነው ያሉት።

በጉድለት የተለዩትና መስተካከል አለባቸው ተብለው በጥናቱ የተገኙት ቀደም ሲል በሎጂስቲክ ስትራቴጂ ከተለዩት ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የዓለም ባንክ መሰል ሰነድ የሚዘጋጀው በየሁለት ዓመቱ መሆኑን ጠቅሰው፤ በየዓመቱ እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ዘርፉን በማዘመን  ጥረት እያደረጉ ላሉ አገራት ዓለም አቀፍ መስፈርትን የተከተለ አገር በቀል ጠቋሚ ቀመር አዘጋጅቶ ሥራ ላይ ማዋል በርካታ ፋይዳ ያለው ተግባር መሆኑንም አስረድተዋል።

የዓለም ባንክ የሎጂስቲክ ደረጃ ሳይጠበቅ ዘርፉን ለማቀላጠፍና በማዘመን ጥረት ሳይንሳዊ በሆነ አተያይ ለመገምገም ማስቻል ከእነዚህ ፋይዳዎች መካከል መሆናቸውን በመጠቆም።

የባለድርሻ አካላት ሚናን የተሳትፎ መጠንና ሊሻሻል የሚገባውን ውስንነት እየገመገሙ ለመሄድ ያስችላልም ብለዋል።

ዲጂታላይዝ ሎጂስቲክ ሥርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑም እንዲሁ።

የአገር ውስጥ የሎጂስቲክ አፈጻጸም ደረጃ ጠቋሚ ቀመር ሰነድን ለመተግበርና ዘላቂነት ያለው የመረጃ ሥርዓት በዘርፉ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ባለድርሻ አካላት እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም