የ2014 በጀት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ስለሰጠ የዋጋ ንረቱን የማረጋጋት ሚናው የጎላ ነው - ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ማሞ ምህረቱ

112

ሰኔ 29 ቀን 2013 (ኢዜአ) የ2014 የመንግስት በጀት ለግብርናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት የሰጠ በመሆኑ የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ።

አማካሪው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በጀቱ ለግብርናው ዘረፍ በተለይም ደግሞ ለመስኖ ፕሮጀክት ሰፊ የካፒታል ወጪ መድቧል።

ይህም ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸው፤ “የተጀመሩ ፕሮጀክቶች እንዲጠናቀቁ በማድረግ የማክሮ ኢኮኖሚውን ያረጋጋዋል” ብለዋል።

በጀቱ በአብዛኛው የሚሰበሰበው ከታክስ በመሆኑ የታክስ አሰባሰብ ስርዓትን ለማዘመን ትኩረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ "ግብር መክፈል ግዴታዬ ነው" የሚል ባህል እንዲያዳብርና ሌሎች አዳዲስ የገቢ አማራጮችን እንዲያሰፉ ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም የበጀት ጉድለት በሚያጋጥምበት ወቅት ከብሔራዊ ባንክ በብድር ለመሙላት ጥረት ይደረግ እንደነበር አስታውሰው፤ “ይህም ለዋጋ ንረት መስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ አድርጓል” ብለዋል።

በ2014 በጀት ዓመት የበጀት ጉድለት በሚያጋጥምበት ወቅት የግምጃ ቤት ሰነድ በመሸጥ የገበያውን ጉድለት ለመሙላት እንደሚሰራም ጠቁመዋል።

በዚህም የዋጋ ግሽበትና የኑሮ ውድነትን ማቃለል እንደሚቻል አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ትናንት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ የዋጋ ንረቱን ለማቃለል በመኸር ወቅት "መሬት ጾሙን ማደር የለበትም" በሚል የእርሻ ስራ በስፋት እንደሚከናወን መግለጻቸው ይታወሳል።

የዋጋ ግሽበትን ለመከላከል ፍላጎትና አቅርቦትን ማመጣጠን፣ የግብይት ሰንሰለቱን ችግር መፍታት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው፤ “በተጨማሪም የበጋ ስንዴ ምርት ላይ ልዩ ትኩረት ይደረጋል” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም